ዋነኛ ተፈላጊ የሆነው ግብጻዊው ጂሀዲስት ሂሻም አሽማዊ ሊቢያ ውስጥ ተያዘ።

ዋነኛ ተፈላጊ የሆነው ግብጻዊው ጂሀዲስት ሂሻም አሽማዊ ሊቢያ ውስጥ ተያዘ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ/ም ) የሊቢያ የደህንነት ኃይሎች ዋነኛውን ተፈላጊ ግብጻዊውን ጅሀዲስት በቁጥጥር ስር ያዋሉት ፣በምስራቃዊዋ የወደብ ከተማ በዳርናህ እያካሄዱት ባለው ዘመቻ ነው።
ቀድሞ የፖሊስ መኮንን የነበረው ሂሻም አሽማዊ ፣ በግብጽ ውስጥ በተፈጸሙ በርካታ የሽብር ጥቃቶች እና የባለሥልጣናት ግድያዎች ፣ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል።.
አብዛኛውን ምሥራቃውን ክፍል የተቆጣጠረው የሊቢያ ብሔራዊ ሰራዊት እንደገለጸው፣ ጂሀዲስቱ ሂሻም ሲያዝ ተቀጣጣይ የቦምብ ቀበቶ ታጥቆ ነበር።
ሊቢያ፣እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 የኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ አገዛዝ መወገዱን ተከትሎ በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት እየተናጠች ትገኛለች። ሰላማዊዋ ምድር ላለፉት ሰባት ዓመታት የሽብርተኞች መናኸሪያ እንደሆነች ዘልቃለች።
ጋዳፊ በአረቡ አብዮት አማጽያንና በም ዕራባውያን ደጋፊዎቻቸው መገደላቸውን ተከትሎ ነው የ40 ዓመቱ የአገዛዝ ዘመናቸው ያከተመው። የቀድሞው የሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስልጣን በለቀቁ ማግስት ባደረጉት ቃለ ምልልስ በስልጣን ዘመናቸው ተፈጽሟል ብለው ስለሚያምኑት ስህተት ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሊቢያ ስህተት ነበር” ማለታቸው ይታወሳል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ የሰሜን አፍሪቃዋ ሀገር በአሁኑ ወቅት በሦስት ተፎካካሪ ኃይሎች ሥር ነች።
የመጀመሪያው መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው እና በመንግስታቱ ድርጅት የሚደገፈው የሽግግር መንግስት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከግብጽ ጋር ጥብቅ ትብብር ያለው፣ በጠንካራው በካሊፋ ሀፍታር የሚመራው እና አብዛኛውን ምሥራቃዊውን ግዛት የተቆጣጠረው የሊቢያ ብሄራዊ መከላከያ ኃይል ነው። ሦስተኛው ቡድን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ካሊፋ ግዌል ስር የሚገኘው ደካማው ብሄራዊ መድህት ድርጅት ነው።
ግብጻዊው ሂሻም አሽማዊ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከግብጽ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ባለው በብሄራዊ መከላከያ ኃይሉ ነው።
ብሄራዊ መከላከያ ኃይሉ ባለፈው ሰኔ ወር ባወጣው መግለጫ የወደቧን ከተማ ዳርናህን ከጂሀዲስቶች ቢያስለቅቅም ከአማጽያኑ መጠነኛ ተግዳሮት እንደገጠመው አስታውቆ ነበር።
ዛሬ በሰጠው መግለጫ ደግሞ፦” ሽብርተኛው አሽማዊ ተቀጣጣይ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ቢታጠቅም ቦምቡ ሳይፈነዳ በቁትጥር ሥር ውሏል። በአሁኑ ወቅት በዳርናህ ከተማ አቅራቢያ ባለችው በአል ማጋር ታስሯል።” ብሏል።
አሽማዊ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ ለግብጽ ባለሥልጣናት ተላልፎ እንደሚሰጥም ብሔራዊ መከላከያ ኃይሉ ማስታወቁንም የሬውተርስ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።
ከሊቢያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይሉ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላት ግብጽ ከጅሀዲስቶች ጋር በዳርናህ የተደረገውን ዘመቻ በአየር ጥቃት ሽፋን በመስጠት ደግፋለች።
እንደ ግብጽ ባለሥልጣናት ገለጻ፣ አሽማዊ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 የሊቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርን መሀመድ ኢብራሂምን ለመግደል ከተደረገው ሙከራ ጀርባ እጁ ያለበት ሲሆን፣በ2015 የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመኪና ላይ በተጠመደ ፈንጅ የተገደሉበትን ሴራ ያቀናበረ ነው።
አሽማዊ፣ ራሱን ኢስላማዊ መንግስት ብሎ ከሚጠራው አይሲስ ጋር ከተለያዬ በኋላ አል ሞራቢቶን የተሰኘና ከአል ቃይዳ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያለው ድርጅት መሥርቶ ነው ሲመራ የቆዬው።
የአሽማዊ ድርጅት ከአልቃይዳ በተጨማሪ “አንሳር አል ኢስላም” እና “ጁንድ አል ኢስላም” ከተባሉት ሁለት የግብጽ ጅሀዲስት ድርጅቶች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው ተመልክቷል።
“አንሳር አል ኢስላም” ባለፈው ዓመት በርካታ ግብጻውያን ፖሊሶች ለተገደሉበት ድንገተኛ የሽብር ጥቃት ኃላፊነት መውሰዱ ይታወቃል።