ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆኑ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 22/2011)ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ።

የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን በመመስረትና በመምራት ለረጅም አመታት ያገለገሉት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ እንስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

አቶ ሰለሞን አረዳ ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በዛሬው እለት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የወሰዱት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ በአሜሪካ ኬንታኪ ዩኒቨርስቲ በአለም አቀፍ ሕግ 2ኛ ዲግሪ ማግኘታቸውም ተመልክቷል።

በከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት በተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች በሕግ አማካሪነት ማገልገላቸው የተገለጸው ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መስራችና ፕሬዝዳንት ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል

የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ዳይሬክተር በመሆን በኢትዮጵያ በተካሄዱ ምርጫዎች የፓርቲዎች የክርክር መድረክ በማዘጋጀትና በሕገመንግስቱ ማርቀቅ ሒደት መሳተፋቸውም ተገልጿል።

በንግዱ አለም ከእናት ባንክ መስራቾች አንዷ የሆኑትና ባንኩንም በቦርድ ሊቀመንበርነት ያገለገሉት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ በሐገሪቱ ያሉ አፋኝና ሌሎችን ሕጎች እንዲመረመር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ውስጥ በምክትል ሰብሳቢነት በማገልገል ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ 4ኛዋ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት የሆኑት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ላለፉት 2 አመታት ያህል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ያሉትን አቶ ዳኜ መላኩን ተክተዋል።

አቶ ተገኔ ጌታነህ ፣አቶ መንበረ ጸሃይ ታደሰና አቶ ከማል በድሪ ቀደም ሲል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነት በኢሕአዴግ ዘመን አገልግለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ጸጋዬ አስማማውን በመተካት አቶ ሰለሞን አረዳ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ተሹመዋል።

አቶ ሰለሞን አረዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያና 2ኛ ዲግሪያቸውን እንዳገኙም በሕይወት ታሪካቸው ላይ ተመልክቷል።

በሕዝብ አስተዳደርና በአለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሕግ ከሃርቫርድና ከአምስተርዳም ዩኒቨርስቲ ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪ ማግኘታቸውም ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በፓርላማ ተገኝተው የሁለቱን እጩዎች ፕሬዝዳንትነት አጽድቀዋል።