ከፊል አውቶማቲክ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ግለሰቦችና የግል ኩባንያዎች እንዳይጠቅሙ ህግ ወጣ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 10/2011) ከፊል አውቶማቲክ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ግለሰቦችና የግል ኩባንያዎች እንዳይጠቅሙ የሚከለክል መመሪያ የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አወጣ።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከመጋቢት23/2018 ጀምሮ መሳሪያዎቹን መጠቀም የተከለከለ በመሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ አምራቾች እንዲያወድሙ አሊያም ለሚመለከተው አካል እንዲያስረክቡትላንት መመሪያ ወጥቷል።

ከአውቶማቲክ መሳሪያዎች ውጭ ከፊል አውቶማቲክና አውቶማቲክ ያልሆኑ መሳሪያዎችን ገዝቶ መታጠቅ በማይፈቀድባት አሜሪካ የአሰቃቂ ግድያዎች እየጨመሩ መምጣት ብርቱ ተቃውሞን ሲያስከትል ቆይቷል።

በተለይም ከአንድ ዓመት በፊት የአሜሪካ የቁማርና የመዝናኛ ማዕከል በሆነችው ላስቬጋስ ከተማ በአንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የነበሩ 57 ሰዎች መገደል በጦር መሳሪያ መጠቀም መብት ዙሪያ ከፍተኛ ውይይት ቀስቅሷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥቅምት ወር 2017 ስቴፈን ፓዶክ የተባለ የ64 ዓመት ሰው ላስቬጋስ ከተማ ከሚገኘው ማንዳሊ ቤይ ሆቴል 32ኛ ፎቅ ላይ ከያዘው መኝታው ክፍል ቁልቁል 22ሺህ ሰው በታደመበት የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በከፈተው ተኩስ 58 ሰዎች ሲገደሉ 489 የሚሆኑት ቆስለዋል።

ፖሊስ ከመድረሱ በፊትም ግለሰቡ ራሱን ያጠፋ ሲሆን በመኝታ ክፍሉ ውስጥም 23 የጦር መሳሪያዎች መገኘታቸው ይታወሳል።

ይህንና መሰል ግድያዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ መመሪያውን ትናንት እንደወጣ መረዳት ተችሏል።

ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ- ማቲው ዋይታከር መመሪያውን የፈረሙ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ ከመጋቢት 23/2018 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

ቀደም ሲልም አውቶማቲክም ሆነ ማሽንጋን መሳሪያዎችን ግለሰቦች እንዳይጠቀሙ ህግ ይከለክላል።

በአዲሱ መመሪያ ከፊል አውቶማቲክ መሳሪያዎችም በዕገዳው ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል።

ሆኖም ሽጉጥና አውቶማቲክ ያልሆኑ መሳሪያዎችን ገዝቶ መጠቀም አልተከለከለም።

አዲሱን ዕገዳ ለማስቀልበስ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ከወዲሁ የተገመተ ሲሆን የመመሪያው አውጪዎች መመሪያው የሃገሪቱን ህግ መሰረት ያደረገ ስለሆነ እንሞግታለን ብለዋል።

ክልከላው በመላው አሜሪና ተፈጻሚ ይሆናል።