ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አማካሪ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

ግንቦት 20 2002 ዓም
ጉዳዩ፡ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዠን ስርጭት መቋረጥን ይመለከታል
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ላለፉት 24 ሰዓታት በአየር ላይ አለመዋሉ ይታወቃል።
የስርጭቱ መቋረጥ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን በሺዎች የሚቆጠሩ የስልክና የኢሜል መልእክቶችን ልከውልናል።
ለተሰጠው የሞራል ማበረታቺያ፣ የበጎ ምኞት መግለጫ ና ድጋፍ ተመልካቾቻችንንና ደጋፊዎቻችንን ማመስገን
እንወዳለን። የኢሳት አማካሪ ቦርድ ለተመልካቾቻችንና ለደጋፊዎቻችን የሚከተሉትን መልእክቶች ማስተላለፍ ይፈልጋል፣
አገልግሎቱ የተቋረጠው ኢሳት በወሰዳቸው ወይም የኢሳት ሰራተኞች በወሰዱት እርምጃ አይደለም። ችግሩ የተከሰተው
ከኢሳት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የቴክኒክ ወይም የመሳሪያ ችግር አይደለም። ኢሳት ችግሩን ና የችግሩን መፍትሄ
በተመለከተ አገልግሎት ከሚሰጠው ድርጅት ጋር በመነጋገር ላይ ነው፣ ችግሮች ካሉም በመመካከርና በትብብር
ለመፍታት እንሞክራለን። የስርጭቱን መቋረጥ በተመለከተ የተለያዩ መላምቶችን፣ግምቶችን፣ አስተሳሰቦችንና እምነቶችን
በመሰንዘር ላይ ለሚገኙ ተመልካቾችና ደጋፊዎች የችግሩ ምንጭ በውል እስከሚታወቅና ይፋዊ መግለጫ እስከሚሰጥ
ድረስ የግል አስተያየቶችን ከመሰንዘር ቢቆጠቡ መልካም ነው እንላለን። ኢሳት የሰርጭት አገልግሎቱን እንደሚጀምር
ለተመልካቾቻችንና ለደጋዎቹ እያረጋገጠ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር ለሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ ዘላቂ
የሆነ የድጋፍ ጥሪ ያቀርባል። በመጨረሻም የሞራል፣ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፎችን ላደረጉ ተመልካቾችና ደጋፊዎች
በሙሉ ኢሳት ምስጋናና አድናቆቱን እየገለጸ፣ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ከጎኑ በመቆም በትእግስት
እንድትጠባበቁ ይጠይቃል።