ከአባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽ እንቅፋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 9/2010)በኢትዮጵያ ከአባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽ እንቅፋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች ነው ሲል የግንባታው ብሔራዊ ምክርቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ግብጽ በበኩሏ በገለልተኛ አለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚቴ ይቀርባሉ የተባሉ ሁለት ጥናቶች በመዘግየታቸው ጉዳዩ ክፉኛ አሳስቦኛል ስትል በመስኖ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች።

በአዳይ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ፣የግብጽና የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ መክረዋል።ግድቡንም ጎብኝተዋል።

የአባይ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን የልማት ተስፋ ለግብጽ ደግሞ የጥፋት ስጋት ሆኖ ሁለቱንም ሀገራት በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርጓል።

አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በአባይ ግድብ ግንባታ ተቃውሞ ባይኖራቸውም ግብጽ ግን ሁኔታውን በጥርጣሬና በአንክሮ ነው የምትመለከተው።

የአባይ ግድብ ግንባታ ብሔራዊ ምክርቤት ጽሕፈት ቤት በእቅድና አተገባበሩ ዙሪያ አጋር ከሚላቸው አካላት ጋር ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሆቴል ምክክር አድርጓል።

በዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ጽሕፈት ቤት ታዲያ ግብጽ ከአባይ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ እንቅፋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች ነው ብሏል።

ሰንደቅ ጋዜጣ ጽሕፈት ቤቱ ያካሄደውን ምክክር ጠቅሶ እንደዘገበው ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ እይታ በተጻረረ መልኩ በግብጽ የሚደገፉ አፍራሽ ሃይሎች ስራውን ለማስተጓጎል እየተሯሯጡ ይገኛሉ።

የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን ሕጋዊ እውቅና እንዳይሰጡ ግብጽ እንቅፋት እየፈጠረች ነው ሲልም ጽሕፈት ቤቱ አቋሙን ገልጿል።

እናም በግብጽ መንግስት እየተካሄደ ያለውን አሉታዊ እንቅስቃሴ ልንመክተው ይገባል ነው ያለው ጽሕፈት ቤቱ በምክክር መድረኩ ባቀረበው ገለጻ።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ የግብጽና የሱዳን መስኖና ውሃ ሚኒስትሮች በግድቡ ግንባታ ዙሪያ በአዲስ አበባ ምክክር አድርገዋል።

ሱዳን ትሪቡን እንደገለጸው የ3ቱም ሀገራት ሚኒስትሮች በአባይ ጉዳይ ላይ መወዛገባቸውን እንደቀጠሉ ነው።

የግብጹ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ሞሀመድ አብደል አታይ ሀገራችን በገለልተኛ አለምአቀፍ ባለሙያዎች ይካሄዳል የተባለው ጥናት መዘግየቱ በእጅጉ አሳስቧታል ብለዋል።

እናም በአማካሪ ጽሕፈት ቤቱ የተዘጋጀውን ሪፖርት ለመቀበል ሀገሬ ይቸግራታል ነው ያሉት።

የ3ቱ ሀገራት ሚኒስትሮች በቅድመ ሪፖርቱና ጥናቱ መነሻ ሀሳቦች ላይ ቢስማሙም ልዩነቱ ግን እንዳለ መሆኑን ኢጅፕት ኢንዲፐንደንት የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ፣የግብጽና የሱዳን ሚኒስትሮች ከአዲስአበባው ውይይታቸው በኋላ ወደ ግድቡ ግንባታ ቦታ በማምራት ጉብኝት አድርገዋል።

የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ጊዜ 60 በመቶ መድረሱንና በዘንድሮው አመት የተወሰነ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ኢትዮጵያ ማመንጨት እንደምትጀምር ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

በአባይ ግድብ ውስጥ ውሃ የመሙላት ስራ እስካሁን አልተጀመረም።–ለግንባታው ያስፈልጋል የተባለው 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላርም እስካሁን ሙሉ በሙሉ አልተሟላም።

አባይ ግድብ ከተጀመረ በ5 አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም ስራው ግን ከተጀመረ 7 አመታት አልፎታል።