ከቀናት በፊት ከእስር የተፈቱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላትን ለመቀበል አደባባይ ከወጣው የአርባ ምንጭ ነዋሪ ውስጥ በርካቶች መታሰራቸው ተገለጸ።

ከቀናት በፊት ከእስር የተፈቱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላትን ለመቀበል አደባባይ ከወጣው የአርባ ምንጭ ነዋሪ ውስጥ በርካቶች መታሰራቸው ተገለጸ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ/ም ) ነሀሴ 8 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ከእስር ከተለቀቁት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አባላት መካከል
የአርባ ምንጭ ልጆች የሆኑትን ወጣት ተካልኝ መንግስቱ እና ወጣት አወቀ ደመቀን በልዩ ድምቀት ለመቀበል የከተማው ነዋሪ አደባባይ መውጣቱ ያስቆጣቸው የህወሓቱ ፖሊስ አዛዥ ኮሎኔል ገብረ ሳሙኤል፣ ፖሊሶች ሕዝቡን እንዲበትኑ በማዘዛቸው ችግር መከሰቱን የዐይን እማኞች ገልጸዋል።
ለወጣቶቹ የጀግና አቀባበል ለማድረግ በአውራ ጎዳና ግራና ቀኝ ሆኖ የተሰለፈውን ሕዝብ ለመበተን ብዛት ያላቸው ፖሊሶች በከተማዋ መፍሰሳቸውን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ሕዝቡም “ጀግኖቻችንን ከመቀበል ውጭ ምን ስላደረግን ነው የምትበትኑን?፡በማለት ሲጠይቅ ታጣቂዎቹ ኃይል መጠቀማቸው ተመልክቷል።
ይህን ተከትሎ ወጣት አወል ሀሰንና ወጣት ውብሸት ጌታቸውን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ወጣቶች መታሰራቸው ታውቋል።
በመንግስት የሰላም ጥሪ እና ድርድር መሰረት በትጥቅ ይታገሉ የነበሩ ድርጅቶች ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የድርሻቸውን ለመወጣት በተዘጋጁበት ወቅት ፣ የለውጥ ሂደቱን ለመቀልበስ የሚሹ የህወኃት አመራሮች አንዳንድ ሙሰኞች ሰላምንና እርቅን በሚያደፈርስ ድርጊታቸው መቀጠላቸው የአርባ ምንጭ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።
“እስከመቼ በፖሊስ እየታፈንን በኃይል ስንገዛ እንኖራለን?” ያሉት የከተማዋ ወጣቶች ፣ የዶክተር አብይ አስተዳደር የለውጥ እንቅፋቶች በሆኑ እንደ ኮሎኔል ሳሙኤል ገብረ ባሉ አዛዦች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
ይሕ በእንዲህ እንዳለ ከእስር የተፈቱት የአርበኞች ግንቦት ሰባት የአርባ ምንጭ ወጣቶች የጀግና አቀባበል ጠብቋቸዋል።