ከሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች አምስቱ ታፍነው ተወሰዱ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 6/2010) ለአቤቱታ አዲስ አበባ ከሚገኙት የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አምስቱ ታፍነው መወሰዳቸው ተገለጸ።

ላለፉት ሁለት ወራት አዲስ አበባ ሆነው በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አፈናና ግድያ እንዲቆም ለመጠየቅ እያደረጉ ያሉት ጥረት በህወሃት ደህንነቶችና የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ባሰማራቸው አፋኝ ሃይሎች ምክንያት ሊሳካ እንዳልቻለ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በህወሃት ደህንነቶች ወከባ እየተፈጸመባቸው ያሉት የሃገር ሽማግሌዎቹ የፌደራል መንግስት ጥበቃ ያድርግልን የሚል ጥሪ እያቀረቡ ባሉበት ጊዜ ነው አምስቱ ሰዎች የታፈኑት።

ወዴት እንደተወሰዱ ለማወቅ እንዳልተቻለም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ የድረሱልን ጥሪ ሰሚ ያገኘ አይደለም ይላሉ ጉዳዩን እየተከታተሉ የሚገኙ የኢሳት ምንጮች።

ባለፈው ሳምንት ከሀገር ሽማግሌዎቹ አንደኛው በአብዲ ዒሌ የተሰማሩ ሰዎች አፍነው ከወሰዷቸው በኋላ ባሰሙት የድረሱልን ጥሪ የፌደራል መንግስት በአፋጥኝ የደህንነት ጥበቃ ያድርግልን ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ሆኖም ጥሪያቸውን ሰምቶ ምላሽ የሚሰጣቸው አካል ባለመኖሩ ተጨማሪ አምስት የሀገር ሽማግሌዎች በትላንትናው ዕለት ታፍነው ወደ አልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሱልጣን ኣብዱላሂ ሞሀመድ፣ኣብፊላሂ ሞሀመድ፣ ኦስማን ሚሬ፣ኢብራሂም ኤግና ማሳላህ ሰይድ የተባሉት የሶማሌ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን አባላት ትላንት ታፍነው የተወሰዱት በህወሀት ደህንነቶችና በሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ በተላኩ አፋኝ ሃይሎች አማካኝነት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የቀሩት የሀገር ሽማግሌዎች ተመሳሳይ የአፈና እርምጃ ይወሰድብናል በሚል በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የት እንደተወሰዱ አናውቅም፡ ህይወታቸው አደጋ ላይ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጹን ያሰማልን ሲሉም ቀሪዎቹ ሽማግሌዎች በኢሳት በኩል መልዕክታቸው እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።

የአብዲ ዒሌ አስተዳደር በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ሰቆቃ እያደረሰ ከመሆኑም ባለፈ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተስማምተን እንዳንኖር እያደረገን ነው የሚሉት 150 የሚሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ቀውሱ ሁላችንንም ወደማንወጣው አደጋ ውስጥ ከማስገባቱ በፊት የክልሉ ፕሬዝዳንት ከስልጣን ይነሱ የሚል አቤቱታ ይዘው አዲስ አበባ ከገቡ 2 ወራት አልፏቸዋል።

እስከአሁን ያናገራቸው አንድም የመንግስት ባልስልጣን የለም።

ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቢሮ ለመጠጋት ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ በህወሀት የደህንነት ሃይሎች አማካኝነት እንዳይሳካ ተደርጓል።

የህወሀት ጄነራሎች ከአብዲ ዒሌ ገንዘብ ተከፍሏቸው ሽማግሌዎቹን ከአዲስ አበባ ለማስወጣት ያደረጉት ሙከራ በሽማግሌዎቹ እምቢተኝነት ባይሳካም ህወሀት በእጅ አዙር ሽማግሌዎቹ ላይ ከፍተኛ ወከባና ማስፈራራት በመፈጸም ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ኢሳት ታፈኑ የተባሉት አምስቱ የሀገር ሽማግሌዎች የት እንዳሉ ለማወቅ ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።