ከሆሊስቲክ ፈተና ጋር በተያያዘ አድማ ያደረጉ ተማሪዎች ታገዱ

ከሆሊስቲክ ፈተና ጋር በተያያዘ አድማ ያደረጉ ተማሪዎች ታገዱ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ/ም ) በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ከሆሊስቲክ ወይም ከማጠቃለያ ፈተና ጋር በተያያዘ ተማሪዎች የጀመሩትን አድማ ተከትሎ ሰኔ 7 ቀን 2010ዓ.ም ከግቢ መባረራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሰሞኑን ከታማኝ ምንጮች የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው ዓመት ሶስተኛ ዓመት የነበሩ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ተማሪዎች በዚህ ዓመት ትምህርት እንዳይከታተሉ የእግድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ታውቋል።
በዩኒቨርስቲው አሰራርና ልምድ በዚህ ዓመት ሶስተኛ ዓመት ያስተማረ መምህር በቀጣይ ዓመት የአራተኛ ዓመት ተማሪዎችን በማስተማር እንደሚቀጥል የሚታወቅ ቢሆንም፣ በዚህ ዓመት የአራተኛ ዓመት ተማሪዎችን የሚያስተምሩ መምህራን ሌላ ምደባ እደተካሄደ አረጋግጠዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም ዩኒቨርስቲው የአራተኛ ዓመት የቴክኖሎጂ ተማሪዎች እንደማይኖሩት፣ በዚህ አሰራር ከቀጠለና አቋሙን ካልቀየረ በ2012 ዓ.ም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ምንም ተመራቂ ተማሪ እንደማይኖር ምንጮች ገልጸዋል።