ኦዴፓ በብሔሮች ራስን የማስተዳደር መብት ላይ አልደራደርም አለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት/2011)በፌደራል ስርዓቱ በብሄሮች ራስን የማስተዳደር መብት ላይ ከማንም ጋር እንደማይደራደር  የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ገለጸ።

ፓርቲው  ባወጣው መግለጫ በፌደራል ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እየተካሄደ ነው ብሏል።

የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እና የአፋን ኦሮሞ ሁለተኛ ብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆንም እየተሰራበት  መሆኑን ኦዲፒ ገልጿል።

ኦዴፓ በአጀንዳነት ይዞ ከሚታገልባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የፌደራል ስርዓቱ ነው ብሏል።

እንደ ድርጅቱ መግለጫ ለፌደራል ስርዓቱ መምጣት ብሄረሰቦች ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል።

እናም የፌዴራል ስርአቱ እና ብሔሮች ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ለድርድር አይቀርብም ነው ያለው ።

በአሁኑ ወቅትም በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የፌዴራል ስርዓቱን ሊያፈርስ እንደሆነ ለማድረግም እየተሰራ ነው ብሏል።

ህብረተሰቡ በፌዴራል ስርዓት ላይ ያለውን እምነት እና ተስፋ እንዲቀንስ ከፍተኛ የሆነ የሀሰት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጿል።

ኦዴፓ እንደሚለው የሀሰት ዘመቻው ሁለት ዓላማ ያለው ነው ።

አንደኛው የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሁን ያለውን ለውጥ በጥርጣሬ እንደሚመለከቱ ማድረግ መሆኑን ነው የገለጸው።

ብሔሮችና ብሄረሰቦች የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ታሪክ ማሳደግን በትግል እና በመስዋዕትነት ያገኙት ቢሆንም የፌደራል ስርዓቱ ሊፈርስ ነው በሚል በጥርጣሬ ተቃውሞ እንዲያስነሱ ታስቦ የሚደረግ ሴራ መሆኑንም ገልጿል።

የኦሮሞን ህዝብ “ተጨማሪ መብት ማግኘት ቀርቶ ከዚህ ቀደም የተገኘውን መብት ልታጣ ነው” በሚል በማደናበር እርስ በርስ ለማጋጨት ያለመ መሆኑንም ኦዲፓ አስታውቋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄን በመግለጽ የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እና የአፋን ኦሮሞ ሁለተኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆንም እየተሰራበት  መሆኑን ኦዴፓ ገልጿል።

ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ላይም ትኩረት በመስጠት እየሰራበት መሆኑን ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።

ኦዴፓ ለተጨማሪ ድል ይሰራል እንጂ ከዚህ ቀደም የተገኙ ድሎችን አያከሽፍም ያለው ፓርቲው፥ በፌደራል ስርዓት ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥ በመግለጫው አስታወቋል።