ኦነግ በምዕራብ ወለጋ የመንግስት ታጣቂዎችን ትጥቅ እያስፈታ ከመሆኑም በላይ ያገታቸው ነጋዴዎች መኖራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ኦነግ በምዕራብ ወለጋ የመንግስት ታጣቂዎችን ትጥቅ እያስፈታ ከመሆኑም በላይ
ያገታቸው ነጋዴዎች መኖራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 01 ቀን 2011 ዓ/ም ) ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት “በኡላ ኖሌ” ወረዳ የኦነግ ታጣቂዎች መንግስት ያስታጠቃቸውን የአካባቢ ሚሊሺያዎችን ትጥቅ በማስፈታት የጦር መሳሪያዎችን ወስደዋል። የኦነግ ታጣቂዎች በዚሁ ወረዳ ጌጡ ገበየሁ የሚባል ታዋቂ ነጋዴን አፍነው የወሰዱ ሲሆን፤ ነጋዴው እስካሁን የደረሰበት አልታወቀም።
ከኖሌ 25 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ጉይ ከተማ ደግሞ የፖሊስ ጽ/ቤትን በመስበር የጦር መሳሪያ መውሰዳቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። በዚሁ አካባቢ ወጣቶችን እየመለመሉ ወታደራዊ ትምህርት በመስጠት እና በማስታጠቅ ላይ መሆናቸውን እንዲሁም አካባቢው ከጋምቤላና ከኢሊባቡር ጋር የሚዋሰን በመሆኑ በዚሁ አካባቢ የጦር መሳሪያ እያስገቡ መሆኑንም ንዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።
በዚሁ አካባቢ ከ2 ሳምንት አፊት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ አንዲት ፖሊስ ተገድላ እንደነበርም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በቡሌ ሆራ ወረዳ ደግሞ የኦነግ ታጣቂዎች በርጅ ማህበረሰብ አባላት ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት አጠናክረው መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በዚሁ ከተማ ከሳምንት በፊት አንድ የፖሊስ ባልደረባ የነበረች ሴት በእነዚህ ታጣቂዎች መገደሏንም የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
መንግስት የኦነግ ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ያቀረበው ጥሪ እስካሁን ተግባራዊ እንዳልሆነ የሚደርሱን ሪፖርቶች ያሳያሉ። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ኦነግ ትጥቁን የማይፈታ ከሆነ መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ እንደሚሰራ በትናንትናው ዕለት ማስጠንቀቅቃቸው ይታወቃል።። ጠ/ሚ አብይ አህመድ በበኩላቸው ኦነግ ትጥቅ አልፈታም አለ የሚባለው የአፍ ወለምታ ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸው በመግለጽ፣ ከድርጅቱ መሪዎች ጋር ሰሞኑን ሲገናኙ በጉዳዩ ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ተናግረዋል።
የቀድሞው የኦነግ አመራር የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ ” ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለቱ እንዳስገረማቸው ለአሃዱ ሬዲዮ ተናግረዋል። አቶ ሌንጮ በሬዲዮው በነበራቸው ቆይታ ፦ “የኦነግ ታጣቂዎች ወጣቱ ከታንክ ጋር ሲጋፈጥ የት ነበሩ? አሁንስ ማንን ሊወጉ ነው ትጥቅ አንፈታም የሚሉት?” በማለት ጠይቀዋል።
አቶ ዳውድ ኢብሳ ትናንት ምሽት ለአሜሪካ ድምጽ ሲናገሩ የኦነግ ታጣቂዎች በመከላከያ ስር ታቅፈው እንዲቀጥሉ ከመንግስት ጋር ስምምነት የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግስት ቃሉን አፍርሶ ማስፈራሪያ መስጠቱን ተቃውሞዋል። ኦቦ ዳውድ አክለውም በስምምነታቸው መሰረት አንዱ ሌላውን ትጥቅ የሚያስፈታበት ሁኔታ እንደሌለ በመግለጽ፤ቀደም ብለው ለዋልታ ቴሌቪዥን የሰጡትን ቃል አጠናክረዋል።