እውቁና አንጋፋው ድምፃዊ፤ አርቲስ ታምራት ሞላ አረፈ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ እንደ ቅርስ ከሚታወቁት አንጋፋ ድምፃውያን አንዱ የሆነው አርቲስት ታምራት ሞላ አረፈ።
ታምራት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ከ 50 ዓመታት በላይ ያገለገለ ስመ-ጥር አርቲስት ነው።
ከዓመታት በፊት በሉኪሚያ (የደም ካንሰር) የተጠቃው ተወዳጁ የባህል ቅርስ፤ከህመሙ ጋር ግብ ግብ ሲያደርግ ከቆዬ በሁዋላ ትናንት ሌሊት በአዲስ አበባ ህይወቱ አልፏል።
በጎንደር ከተማ የተወለደው እና ገና በወጣትነት በሠራዊቱ ውስጥ ሙዚቃን የጀመረው አርቲስት ታምራት በሙያው በቆየባቸው ረዥም ዓመታት ለ አገሩና ለህዝቡ ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከተና የህዝብ ልጅነቱን ያስመሰከረ ድንቅ አርቲስት መሆኑን አድናቂዎቹ ይመሰክሩለታል።
ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከሞት አይቀርምና ፦ <<ስንዋደድ ከልባችን--መሞት ኖሯል ለካስ-መሀላችን>> እያለ ያቀነቀነው አንጋፋው አርቲስት በስተመጨረሻ ወደማይቀርበት ዓለም ተሰናብቷል።
የ አርቲስቱ የቀብር ሥነ-ስርዓት ቤተሰቦቹ፣አድናቂዎቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በዛሬው እለት እንደሚፈጸም ታውቋል።
አርቲስት ታምራት ባለትዳርና የ4 የልጆች አባት ነበር።