ኤች አር 128 ለድምጽ አሰጣጥ ሊቀርብ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2010)

ኤች አር 128 በመባል የሚታወቀውና በአሜሪካ ምክር ቤት የወጣው ረቂቅ ሕገ ውሳኔ በምክር ቤቱ ለድምጽ አሰጣጥ እንደሚቀርብ ታወቀ።

ሕገ ውሳኔው ለድምጽ አሰጣጥ የሚቀርበው በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት መርማሪዎች በሀገሪቱ እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያጣሩ እስከሚቀጥለው ወር ድረስ የማይፈቅድ ከሆነ ነው።

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል ከሌሎች የማህበረሰቡ ተወካዮችና ድርጅቶች ጋር በመሆን ትላንት ከአሜሪካ ምክር ቤት አባላትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ ጋ ኤች አር 128 ሕገ ውሳኔ ስለሚጸድቅበት መንገድ ተወያይተዋል።

ውይይቱ በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የአብላጫ ወንበር ያለው የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ኬቨን ማካርቲ ከኢትዮጵያውያኑ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር በጠየቁት መሰረት የተካሄደ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

በቀጣዩ ወር ማለትም እስከ የካቲት 8 ድረስ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን በሃገሪቱ ገብቶ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ ፍቃድ እንዲሰጥ ቀነ ገደብ ለማስቀመጥ ስምምነት ላይ መደረሱን የውይይቱ ተሳታፊዎች ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

አገዛዙ ለዚህ የማይተባበር ከሆነ ግን ኤች አር 128 በመባል የሚታወቀውና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበርና የመብት ጥሰት የፈጸሙትን በሕግ ተጠያቂ የሚያደርገው ሕግ በአሜሪካ ምክር ቤት እንዲጸድቅ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።

የሕገ ውሳኔው ዋና አዘጋጅ የሆኑት የምክር ቤቱና የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ አባል ክሪስ ስሚዝ የተባበሩት መንግስታት መርማሪዎች ሙሉ ለሙሉ በፈለጉበት ቦታ ተንቀሳቅሰው የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲያጣሩ አገዛዙ የማይፈቅድ ከሆነ ሕጉ በአስቸኳይ ይጸድቃል ብለዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ክሪስ ስሚዝ እንዳሉት በመብት ጥሰቱ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችን በአለም አቀፉ ማግንትስኪ የሰብአዊ መብት ሕግ መሰረት በሕግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ሌላው የምክር ቤት አባል ማይክ ኮፍማን እንዳሉት ደግሞ አሜሪካ ለረጅም ጊዜ ከአገዛዙ ጋር ይላትን የጸጥታ ትብብር ሰበብ በማድረግ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ችላ ስትል መቆየቷ አግባብ እንዳልነበር ተናግረዋል።

አገዛዙ ሕዝቡን እያሸበረ አሜሪካ ትብብሯን መቀጠሏ አግባብ አይደልም ሲሉ ተደምጠዋል።

በኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል ተወካይ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ በበኩላቸው በውይይቱ ወቅት በምክር ቤቱ የአብላጫ ወንበር ያለው የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ኬቨን ማካርቲ እንደተገኙና እሳቸውም በኢትዮጵያ ያለውን የመብት ረገጣ በቅርብ እንደሚከታተሉት ገልጸውላቸዋል።

ኬቨን ማካርቲ ሕጉን የማስቆም ፍላጎት እንደሌላቸው ይሁን እንጂ አገዛዙ አንድ እድል እንዲሰጠው እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ብለዋል።

በዚህም መሰረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪዎች ፍቃድ የማያገኙ ከሆነ ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካይም አገዛዙ ለጥያቄው አዎንታዊ መልስ የሚሰጥ ከሆነ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ወዲያውኑ የማጣራት ስራቸውን እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።