ኢትዮጵያ ለሚቀጥለው አመት ከቀረበው በጀት የ54 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዳጋጠማት ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 1 ፥ 2009)

ለ2010 አም በጀት ከቀረበው የ321 ቢሊዮን ብር ውስጥ የ54 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ማጋጠሙን የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሃሙስ ገለጸ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተያዘው ሳምንት በሃምሌ ወር ለሚጀምረው ቀጣዩ በጀት 321 ቢሊዮን ብር በጀት ማቅረቡ ይታወሳል።

በዚሁ በጀት ዙሪያ ለፓርላማ ማብራሪያ ያቀረበቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ለበጀቱ ከተያዘው ገንዘብ ውስጥ የ54 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት መኖሩን አስታውቀዋል።

ይህንኑ የበጀት ጉድለት ለመሙላት መንግስት ከሃገር ውስጥ ብድር ገንዘቡን ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርግ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።

የምጣኔ ባለሙያዎች በበኩላቸው በየአመቱ ጭማሪን እያሳየ የመጣው የበጀት ጉዳለት በኢኮኖሚ እንቅስቃው እንዲሁም በዋጋ ግሽበት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይገልጻሉ።

ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ሃገሪቱ ያጋጠማትን የበጀት ጉዳለት ከውጭ ሃገር በሚገኝ ብድር እና ድጋፍ ለመሙላት እቅድ ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና የአለም ባንክ ኢትዮጵያ ለተለያዩ ጉዳዮች ከአለም አቀፍ የአበዳሪ አካላት የምትወስደው ብድር ጫናን እያሳደረገ ነው በሚል በብድር ፖሊሲ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ሲያሳሰብ ቆይቷል።

ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ቀጣዩ አመት ያጋጠመው የበጀት ጉድለት ለመሙላት ገንዘቡን ሙሉ ለሙሉ ከሃገር ውስጥ ብድር ለማግኘት እቅድ መያዙን ገልጸዋል።