ኢሶዴፓ የፓርቲውን ስያሜ እና የመተዳደሪያ ደንብ እንደሚያሻሽል ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 30/2011) የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የፓርቲውን ስያሜ እና የመተዳደሪያ ደንብ እንደሚያሻሽል ተገለጸ።

የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ አህመደ ሺዴ  ጉባኤው ፍትህ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደርን በዘላቂነት በክልሉ ለማረጋገጥ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር አቶ አህመደ ሽዴ  እንዳሉት በተመዘገበው ሃገራዊ ለውጥ በክልሉ ጠንካራና ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ ተደርጓል።

በዚህም መቀመጫቸውን በውጭ ሃገር ያደረጉ እንደ ኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ያሉ ያሉ ታጣቂ ሃይሎች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን አስታወሰዋል።

በዚህ ጉባኤም በብቃትና በእውቀት የሚሰሩ በቂ አመራሮችን ወደ ፊት ማምጣት እንደሚገባ ነው የጠቀሱት ። ለዚህም መላው የፓርቲ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ባለፈም ሴቶችን በአመራርነት በማካተት አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

በክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጦፋ አህመድና በፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አህመድ ሼዴ መካከል የነበረው ልዩነት በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት መፈታቱ ይታወሳል። እናም በሁለቱ መካካል የሀሳብ ልዩነት እንጂ መሰራታዊ ግጭት እንደሌለ መናገራቸው ነው የተገለጸው።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም፥ የሶማሌ ክልል ህዝብ የሃገሪቱን ታሪክ አብሮ የጠበቀና አኩሪ ታሪክ ያለው ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተደረገው እንቅስቃሴም አፈናና ሙስናን በማስወገድ አንጻራዊ ሰላምና የዜጎችን በነጻነት የመናገር መብት ማስከበር መቻሉን ጠቅሰዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የሃገር ውስጥና የጎረቤት ሃገራት አጋር ፓርቲ ተወካዮችም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመክፈቻው ላይ ኢሶዴፓ በክልሉ ሙስናን እና አፈናን በማስቀረት ልማትና ሰላምን ለማምጣት ያደረገውን ጥረት የሚያሳዩ የተለያዩ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

ከዚህ ቀደም በክልሉ የነበረው ሁኔታ ሃይልን መሰረት ያደረገ እንደነበርም በዚህ ወቅት ተገልጿል።

በጉባኤው የ ከፓርቲው ስያሜ እና መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ ውይይት እንደተደረግም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ጉባኤ ሁለተንተናዊ ለውጥ ለክልሉ ፍትህና አንድነት የጉባኤው መሪ ቃል ሲሆን እስከ ፊታችን ረቡዕ ድረስ እንደሚቆይ መገኛኛ በዙሀን ዘግበዋል።