ኢህአዴግ በሙስሊሙ ተቃውሞ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መግባቱ ታወቀ

ታህሳስ  ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢሳት ከኢህአዴግ ምንጮች ለመረዳት እንደቻለው ግንባሩ በየጊዜው እያየለ የመጣውን የሙስሊሞችን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የመ-=  ፍትሄ ሀሳብ በማጣቱ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደወደቀ ታውቋል። የመጅሊስ አመራሮች ከተመረጡ እና መሪዎቹ ወደ እስር ቤት ከተጓዙ በሁዋላ እንቅሰቃሴው ይዳከማል የሚል እምነት ይዞ የነበረው ኢህአዴግ፣ እንቅስቃሴው በተቃራኒው እየጨመረ እና የአብዛኛውን ሙስሊም ድጋፍ እያገኘ መምጣቱ ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሎታል።

በግንባሩ ውስጥ እንቅስቃሴው እየጨመረ ይሄዳል የሚል እምነት መያዙን ለማወቅ ቢቻልም፣ እንቅስቃሴውን ለማቆም ምንም አይነት አቅጣጫ እስካሁን አለመያዙን ለማወቅ ተችሎአል።

የሙስሊሞች እንቅስቃሴ በመጪው የወረዳ እና የአካባቢ ምርጫ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል በሚል ኢህአዴግ ዛሬ በተለያዩ እርከን ላይ የሚገኙ አመራሮችን በመሰብሰብ መመሪያ አስተላልፎአል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አወያዮቹ ትኩረት ሰጥተው የተወያዩበት የሙስሊሙ እንቅስቃሴ በመጪው ምርጫ ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ ነው። መንግስት አብዛኛው ሙስሊም አድሞ በመጪው ምርጫ ላይ ድምጽ ለመስጠት አይመዘገብም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህንኑ ለመቀልበስ የዛሬው ስብሰባ መጠራቱ ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት በተጀመረው የመራጮች ምዝገባ እስካሁን የተመዘገበው መራጭ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ፣ የወረዳ ባለስልጣናት፣ የአንድ ለአምስት አባላት፣ እንዲሁም የተለያዩ ማህበራት ቤት ለቤት እየዞሩ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሙስሊሞችን ጨምሮ አብዛኛው ህዝብ ወጥቶ እንዲመዘገብ እንዲያደርጉ ጥብቅ መመሪያ ተላልፎላቸዋል።

ሙስሊሞቹ ህዝቡ እንዳይመዘገብ ጥሪ ከማስተላለፋቸው በፊት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተመዝግቦ ማለቅ አለበት የሚል መመሪያ የወረደላቸው የወረዳ ሹሞች፣ ከነገ ጀምሮ ቤት ለቤት እየዞሩ ህብረተሰቡ እንዲመዘገብ ግፊት ያደርጋሉ።

ህብረተሰቡ ተመዝግቦ በምርጫው ቀን ድምጽ ባይሰጥስ በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ምንጫችን፣ “ኢህአዴግን የሚያሰጋው የመራጩ ቁጥር እንዳይቀንስ ነው እንጅ፣ በእለቱ ድምጽ ሰጠ አልሰጠ የሚለው አይደለም፣ በየቦታው የተሰገሰገው የኢህአዴግ ካድሬ ድምጾችን ኮሮጆ ውስጥ ለመክተት አይሰንፍም።'” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ 33 የፖለቲካ ድርጅቶች ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ፣ ቦርዱን የሚአወግዝ መግለጫ አውጥተዋል።

33 የአዳማ ቴትሽን ፈራሚ ፓርቲዎች በመግለጫው ” የምርጫ ቦርድ የተጣለበትን አገርና የህዝብ ሀላፊነት ወደ ጎን በመግፋት ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ለማድረግ የመወዳደሪያ ሜዳውን ከማስተካከል ይልቅ የገዢው ፓርቲ ወገንተኝነቱን ጉዳይ ፈጻሚነቱን ባረጋገጠበት አቋሙ በመግፋት ወደ ምርጫ እንቅስቃሴ መግባቱን በይፋ አውጃል ” ብሎአል።

“ምርጫ ቦርድ በኢህአዴግ እየተመራና እየታገዘ ከጊዜ ሰሌዳ በፊት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ይቅደም በማለት 41 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዳማው ስብሰባ ላይ ላቀረብነው የቦርዱ ሰብሳቢ ” የውይይት መድረክ ይዘጋጃል” በማለት የመለሱትን እንዲሁም፣ እንዲሁም 33 በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የምንታገል የፖለቲካ ፓርቲዎች ፔትሺን ፈርመን ላቀረብነው የቦርዱ ጽ/ቤት ሀላፊ ” ባትጠይቁንም ማድረግ ያለብን ነው፤ ጉዳዩን ሳታጮሁት በትእግስት ጠብቁ ማለታቸውን ክደው፣ ከአዳማ በተመለሱ በ4ኛው ቀን አጸደቀን ባሉት የጊዜ ሰሌዳ ገፍተውበታል” የሚሉት ፓርቲዎቹ ” ቦርዱ መዝግቤ የምስክር ወረቀት ሰጠሁ ብሎ ከሚዘረዝራቸው 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 28ቱ ብቻ የምርጫ ምልክት ከወሰዱ በሁዋላ የምርጫ ምልክት መውሰጂያ ጊዜ አልፎአል፣ የመምረጫ ጊዜ አልፏል ከማለት አልፎ የህዝብ ታዛቢዎች አስመርጨ የመራጮች ምዝገባ ጀምሬአለሁ ፣ በቀጣይም በጊዜ ሰሌዳየ መሰረት እቀጥላለሁ የሚል ዘመቻውን ተያይዞታል” በማለት ክስ አሰምተዋል።

ፓርቲዎቹ በመጨረሻም ” ምርጫ ቦርድ በኢህአዴግ አይዞህ ባይነት በያዘው ” ካፈርኩ አይመልሰኝ”አቋም መግፋቱ በጥያቄያችን መሰረት የምርጫ መወዳደሪያ ሜዳውን የሚያስተካክል ስላልሆነ በቀጣይ ተወያይተን የምናሳውቃችሁን የጋራ አቋም በንቃት እንድትጠብቁ ” ብሎዋል።

ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ተቃዋሚዎች በምርጫው የማይሳተፉት ከምርጫው በሁዋላ ጥቅም ስለማያገኙበት ነው በማለት መናገራቸው ይታወሳል።