“አገራችን በጥሩ እጅ ላይ ወድቃለች” ሲሉ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ

“አገራችን በጥሩ እጅ ላይ ወድቃለች” ሲሉ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 17 ቀን 2010 ዓ/ም) የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ይህን የተናገሩት በቤተመንግስት የመሸኛ ዝግጅት በተደረገላቸው ወቅት ነው። አቶ ሃይለማርያም ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ያላቸውን አድናቆት ከገለጹ በሁዋላ በአገሪቱ እየነፈሰ ያለው የለውጥ ንፋስ ህዝቡ በሚፈልገው መሰረት እንዲከናወን ከፍተኛ ትግል ያስፈልጋል ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ ነው፡፡ ለውጡ የሁላችንንም ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን ልንረባረብ ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህን ጥሩ የለውጥ ንፋስ አቅጣጫ የሚያስቀይር ከሆነ ወደ አስከፊና የማንወጣበት ነገር ሊያስገባን ይችላል” ሲሉ አቶ ሃይለማርያም አስጠንቅቀዋል። ለውጡ የተወሰኑ ቡድኖችን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ፍላጎት ማእከል ያደረገ መሆን እንደላበትም አክለው ተናግረዋል።
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚገጥማቸው የተናገሩት አቶ ሃይለማርያም፣ ህዝቡ ጊዜ ሊሳጣቸው እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አቶ ሃይለማርያም እርሳቸው ጠ/ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት በታክሲ እንዲሄዱ ያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል።
አቶ ሃይለማርያም በስልጣን ዘመናቸው ወቅት ደካማ መሪ ተደርገው በህዝብ ዘንድ ይቆጠሩ ነበር። የመለስ ዜናዊን ሌጋሲ ለማስቀጠል ወደ አመራር ቦታ መምጣታቸውን ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ መናገራቸውን ተከትሎ፣ በንግግራቸው ሳይቀር አቶ መለስ ዜናዊን ለመመሰል ጥረት ሲያደረጉ በመታየታቸው ብዙዎቹ ይተቿቸው ነበር።
በሽኝኝት ስነስርዓቱ ላይ ዶ/ር አብይ አህመድ የአቶ ሃይለማርያምን ስራዎች በማጉላት ገጽታቸውን የሚገነባ ንግግር አድርገዋል። አቶ ሃይለማርያም በጣት ከሚቆጠሩ ከሙስና ከጸዱ ንጹህ ከፍተኛ ባለስልጣናት ውስጥ አንዱ ናቸው ብለዋቸዋል።