አዴፓና ደኢህዴን መሪዎቻቸውን መረጡ

አዴፓና ደኢህዴን መሪዎቻቸውን መረጡ
( ኢሳት ዜና መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ/ም ) የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተብሎ የተሰየመው ብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን በሊቀመንበርነት እንዲሁም የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን በምክትል ሊቀመንበርነት በመምረጥ ጉባኤውን አጠቃሏል። ድርጅቱ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ አቶ ተፈራ ደርበው፣ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ አቶ መላኩ አለበል፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ አቶ ላቀ አያሌው፣ አቶ ዮሃንስ ቧ ያለው፣ አቶ ጸጋ አራጌንና አቶ ንጉሱ ጥላሁንን በስራ አስፈጻሚነት መርጧል።
ብአዴን ለ5 ቀናት ያደረገውን 12ኛው የድርጅቱ ጉባኤ ሲጠናቀቅ ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ እንደተናገሩት “ የአማራ ህዝብ ባለፉት ጊዚያት በነበሩ የአስተምህሮ አካሄዶች እዳ ከፋይ፣ ባለእዳ መስሎ እንዲታይ፣ ከሌሎች በተለዬ ተጠቃሚ ባልሆነበት ተጠቃሚ መስሎ እንዲፈረጅ በልዩ ልዩ የትውልድ የጉልደት ተሸካሚ መስሎ እንዲታይ የተደረጉ አካሄዶች ነበሩ። ከዚህ ጋር የተያያዙ ማንኛውም ጉዳዮች በትክክለኛ የታሪክ ገጽታው፣ የታሪክ ትርክት የማረቅ፣ የማረምና የማስተካከል ስራ በድርጅቱ መሪነት እና በታሪኩ ባለቤት ተዋናይነት መሰራት ያለበት መሰረታዊ ጉዳይ ነው።” ብለዋል።
አዴፓ ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ ለውጡን ለመቀልበስ የሚደረጉ ሙከራዎችንና ለውጡን የሚፈታተኑ ማናቸውንም ድርጊቶች እንደማይቀበል፣ ነጻነትና ስርዓት አልበኝነት አብረው የማይሄዱ በመሆናቸው ለውጡን ለማስቀጠል ህግ የማስከበር ስራውን እንደሚሰራ ገልጿል።
ከሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ የተደረገው ስምምነት ስህተት ያለው በመሆኑ ፌደራል መንግስቱ የማስተካከያ ስራ እንዲሰራ ጉባኤው ውሳኔ አሳልፏል።
ደኢህዴን በበኩሉ ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚልን የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን ደግሞ ምክትል ሊ/መንበር አድርጎ መርጧል። አቶ ሞገስ ባልቻ፣ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው፣ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ፣ አቶ መለስ አለሙ፣ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም፣ አቶ ጥላሁን ከበደ፣ አቶ አብርሃም ማርሻል ሎውን ጨምሮ 14 ሰዎችን የስራ አስፈጻሚ አድርጎ መርጧል፡፡
ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በነገው እለት ጉባኤያቸውን በአዋሳ ከተማ ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።