አቶ አህመድ ሽዴ ወንጀል ለሰሩ የቀድሞ አመራሮች ከለላ ሲሰጡ ነበር ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2011)የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሶማሌ ክልል ወንጀል የሰሩ የቀድሞ አመራሮች ለህግ እንዳይቀርቡ ከለላ ሲሰጡ እንደነበር የሶማሌ ክልል መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ፕሬዝዳንት የሚዲያ አማካሪ አቶ አብዱላሂ ሁሴን ለኢሳት እንደገለጹት በአቃቤ ህግ የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸውን አመራሮችን ጭምር በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደረገውን እንቅስቃሴ ያስቆሙት አቶ አህመድ ሽዴ ናቸው።

በሌላ በኩል በአቶ አህመድ ሽዴ እህት ኩባንያ ስም ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የሚያሳይ ሰነድ ወጥቷል።

በሰነዱ እንደተመለከተው በሁለት ዙር ክፍያው የተፈጸመ በድምሩ የ52 ሚሊየን ብር ኮንትራት ከሶማሌ ክልል የመስኖ ቢሮ ጋር ስምምነት ተደርሷል።

ስራው ሳይጠናቀቅ ገንዘቡ ሙሉ በሙሉ መከፈሉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የሚዲያ አማካሪ እንደሚሉት ሰሞኑን ሁከትና ብጥብጥን አስታከው ወደ ስልጣን ዳግም ለመምጣት የሞከሩት የቀድሞ አመራሮችን በህግ ለመጠየቅ ተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጓል።

እነዚህ ግለሰቦች በሰሯቸው ወንጀሎች ተጠርጥረው በጠቅላይ አቃቤ ህግ ሳይቀር የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው እንደነበር የሚገልጹት የሚዲያ አማካሪው አቶ አብዱላሂ ሁሴን ህጋዊ ርምጃውን ሲገድቡት የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ ናቸው ብለዋል።

ለክልሉ የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ በመደወል ጭምር ለተጠርጣሪዎቹ ከለላ ሲሰጡ ቆይተዋል ሲሉም ገልጸዋል።

በአቶ አህመድ ሽዴ ከለላ ሲሰጧቸው ከነበሩት አመራሮችና ወደ ውጭ ሃገራት ከሸሹት ጋር በመሆን ክልሉን የማተራመስ ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ አብዱላሂ የህግ የበላይነትን በማስከበር ክልሉን ለማረጋጋት በተደረገው እንቅስቃሴ የአቶ አህመድ ሸዴ ሚና አሉታዊ ነበር ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በአቶ አህመድ ሸዴ እህት በወይዘሮ ካድራ ሸዴ ስም የሚንቀሳቀሰው ተቋራጭ ኩባንያ ከክልሉ መስኖ ልማት ቢሮ ጋር ተፈራርሞ ያላስረከበው የ52 ሚሊየን ብር ኮንትራት መኖሩ ተጋልጧል።

ኢሳት ያገኘው ሰነድ ላይ እንደተመለከተው በሁለት ዙር ክፍያ የወይዘሮ ካድራ ድርጅት ለሆነው ዋርሳሜ ጠቅላላ ተቋራጭ ኩባንያ ሙሉ ገንዘብ ወጪ ተደርጓል።

ስራው ሳይጠናቀቅ ገንዘቡ ወጪ ተደርጎ እንዲከፈል የአቶ አህመድ ሽዴ እጅ እንዳለበት ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።

ወይዘሮ ካድራ ሽዴ የክልሉ ጤና ቢሮ ሰራተኛ ሲሆኑ በየወሩ የመንግስት ደሞዝ እንደሚከፈላቸውም ታውቋል።

ይህንን በተመለከተ ምርመራ ስለመጀመሩ የክልሉ ፕሬዝዳንት የሚዲያ አማካሪ ማረጋጋጫ ባይሰጡም ጉዳዩ እንደሚታወቅ ግን ለኢሳት ገልጸዋል።

አቶ አህመድ ሽዴ በሶማሌ ክልል መንግስት በኩል የሚቀርብባቸው ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ዛሬ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካልን አልቻለም።