አቶ መለስ ዜናዊ በሽብር ተጠርጥረው በታሰሩት ሰዎች ላይ በቂ ማስረጃ አለን አሉ፤ በሌሎችም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ኢሳት ዜና:- አቶ መለስ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት በመድረክ አመራር ውስጥ በርካታ የአሸባሪ ቡድኖች አባላት አሉ  ብለዋል።

እንደርሳቸው ገለጣ የአሸባሪ ቡድኖች የተባሉት የኤርትራ መንግስት፣ ግንቦት7፣ ኦነግ፣ ኦብነግና በአገር
ውስጥ በህጋዊ ሸፋን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች ናቸው።

አቶ መለስ እንደሚሉት በሽብር ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ግለሰቦች ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት የሚያሳዬው ማስረጃ በቅርቡ ለፍርድ ቤት ይቀርባል።

የስዊድን ጋዜጠኞች እንደ ኢትዮጵያውያኑ ሁሉ በእኩልነት በአሸባሪነት እንደሚከሰሱና ጉዳያቸው በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚታይ ተናግረዋል።

በተለመደው የብስጭትና የድካም መንፈስ ውስጥ ሆነው ንግግራቸውን ያቀረቡት አቶ መለስ፣ በአገር ውስጥ ለሚገኙ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በተለይ ጋዜጠኞችን ጋጠወጦች በማለት እስከ መሳደብ መድረሳቸው የጋዜጣ አሳታሚዎችን ማበሳጨቱ ታውቋል።

የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና አሳታሚ የሆነው ወጣት ተመስገን ደሳለኝ አንድ ሰው ስልሳ አመት ከሞላው በሁዋላ ተሳዳቢ ይሆናል ብዬ አላስብም ነበር ብሎአል።

ተመስገን አያይዞ ሲናገር የአቶ መለስ ንግግር አንዳንድ ጋዜጦችን ለመዝጋት መፈለጋቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው።