አቶ መለስ ዜናዊ ሞተውም በከፍተኛ እጀባ እተጠበቁ ነው

መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አራት ኪሎ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ለተቀበሩት ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ መለስ ዜናዊ  ልዩ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ፍኖተ-ነፃነት ዘገበ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታተም ቢከለከልም  “ኦን ላይን” ጋዜጣ በመሆን  በኢንተርኔት ስርጭቱን የቀጠለው ፍኖተ-ነፃነት እንደዘገበው፤ አቶ መለስ ከተቀበሩ በኋላ ባልተለመደ ሁኔታ የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በሮች የተቆለፉ ሲሆን፤ መቃብራቸው በተለየ ኃይል ልዩ ጥበቃ እየተደረገለት ነው፡፡

ከቀብሩ በኋላ በወወክማ ወይም በመንፈሳዊ ኮሌጁ አቅጣጫ ያለው በር ሙሉ በሙሉ ተቆልፎ የሚውል ሲሆን ፤ቀን ቀን በዋናው በር ወደ ቤተክርስቲያኑ የሚገባ ካለ ፤የት እንደሚሄድና  ለምን መግባት እንደፈለገ ተጠይቆ ከታመነበት ብቻ እንደሚገባ እንዲያም ሆኖ ሲገባና ሲወጣ ከትትል እንደሚደረግበት የጋዜጣው ዘገባ ያመለክታል

ምሽት ላይ ዋናው በር  ተከፍቶ በርካታ ሰው ለፀሎት የሚገባ ቢሆንም ፤የአቶ መለስ የቀብር ቦታ በልዩ ጥበቃ እየተጠበቀ ይታያል፡፡

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ላለፉት 21 ዓመታት  በከፍተኛ እጀባና ጥበቃ ያለ ነፃነት  ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል።

በምርጫ 97 ወቅት አርቲስት ደበበ እሸቱ ቅንጅትን በመወከል ባደረገው የምርጫ ቅስቀሳ ፦”ቅንጅት ቢያሸንፍ አቶ መለስ ነፃ ይወጣሉ፤ከሰው ተቀላቅለው ይውላሉ፤ያለ አጃቢ የፈለጉበት ሱቅ ገብተው ሲጃራ መግዛት ይችላሉ” ማለታቸው ይታወሳል።

ይሁንና የምርጫው ውጤት ተቀልብሶ የኢህአዴግ ሥርዓት በመቀጠሉ፤አቶ መለስ  ከሞቱም በሁዋላ ነፃነት ሊያገኙ አለመቻላቸው ተመልክቷል።

በሌላ በኩል በአቶ መለስ ቀብር ዕለት አስክሬኑ የለበሰው ሰንደቅ ዓላማ አብሮ መቀበሩ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን የፍኖተ ዘገባ አመልክቷል።

<<ሰንደቅ ዓላማ ከአስክሬን ጋር ይቀበራልን?>>በማለት የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ያነጋገራቸው  የመዲናይቱ ነዋሪዎች ፦  “ድርጊቱ፤የኢህአዴግ መንግስት በአገር ሰንደቅ ዓላማ ላይ ሲፈጽም ከቆየው ጥፋት አሁንም አለመላቀቁ የታየበት ነው፡፡ የአንድ ሉዓላዊ አገር ባንዲራ አይቀበርም>>ብለዋል።

<<ማንም ይሙት ማን  ባንዲራ አብሮ የሚቀበርበት ህግ የለም፡፡  በአቶ መለስ ቀብር ይህ በመደረጉ  ታሪካዊ ወንጀል ተፈጽሟል”  ሲሉም  አክለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ መለስ ከሁለት ወር በላይ ያሉበት ሁኔታ ሳይታወቅ መቆየቱና  ሞቱ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ አስክሬናቸው እንደ አንድ የአገር መሪ በግልጽ በመስታወት አለመታየቱ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።

ለፍኖት አስተያዬታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፦“ኢህአዴግ የአቶ መለስን መታመም ለብዙ ጊዜ ደብቆን ቆይቷል፡፡ መሞታቸውንም  ከነገረን በኋላ ህክምናቸውን ሲከታተሉበት የነበረውን ሆስፒታል ደበቀ፡፡በሁዋላም  የህክምና ማስረጃቸውን ይፋ አላደረገም፡፡ከዚህም አልፎ ተርፎ አስክሬናቸውንም አላሳየንም፡፡ ከተቀበሩም በኋላ አስክሬኑን በልዩ ሁኔታ እያስጠበቀ ነው።ይህ ሁሉ ለምን አስፈለገ? ከአስክሬኑ ሳጥን ጀርባ ምን ምስጢር አለ?” ሲሉ  ያደረባቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የመቀሌ ነዋሪዎች የአቶ መለስ አስክሬን በግልጽ እንዲታይ ያልተፈለገበት ምስጢሩ ምንድ ነው? የሚል ጥያቄ አንስተው እንደነበር ጋዜጣው አስታውሷል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide