አቶ መለስ በሳልቫኪር አቋም መበሳጨታቸው ተሰማ

ጥር 26 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አቶ መለስ ዜናዊ ደቡብ ሱዳንና ሰሜን ሱዳንን ለመሸምገል ያቀረቡት የሰላም ሀሳብ በደቡብ ሱዳናዊያን ውድቅ በመደረጉ መበሳጨታቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚያዉቁ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለኢሳት ገልጡ።

በቅርቡ ነጻ የወጣችው ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ሱዳን ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ወደ ሰሜኑ የሚሄደውን የነዳጅ ዘይት አቋርጧለች። የደቡብ ሱዳን ውሳኔ በሰሜን ሱዳን ህዝብ ህልውና ላይ የተቃጣ በመሆኑ አገራቸው ደቡብ ሱዳንን ለመውረር እንደምትገደድ የሰሜን ሱዳኑ መሪ ጄኔራል አልበሽር ለህዝባቸው መግለጫ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ጊዜ በሰሜን ሱዳን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ሲሆን፣ ህዝቡም ኑሮውን ሊቋቋመው አለመቻሉን እየገለጠ ነው።

የደቡብ ሱዳን ውሳኔ ሰሜን ሱዳንን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም በቀጥታ የሚመለከትበት ሁኔታ ተፈጥሮአል። ኢትዮጵያ   ከሰሜን ሱዳን ጋር የነዳጅ አቅርቦት ስምምነት ያደረገች በመሆኑና የደቡብ ሱዳን ውሳኔ የኢትዮጵያን የነዳጅ አቅርቦት በቀጥታ የሚወስን በመሆኑ አቶ መለስ ዜናዊ ሁለቱን ሀይሎች ለማስታረቅ ሽምግልና መጀመራቸው ይታወቃል።

አቶ መለስ ያቀረቡት የሰላም ስምምነት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ የደቡብ ሱዳኑ መሪ ሳልቫ ኪር ውድቅ አድርገውታል።

ሳልቫኪር ከሰሜን ሱዳን ጋር የሚኖረው ስምምነት ነዳጅን ብቻ ሳይሆን፣ የድንበር ማካለልን እና  የአቤየ ግዛትን መወሰኑን ማካተት አለበት የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።

ሳልቫኪር ባቀረቡት ሀሳብ የሚገፉበት ከሆነ በሰሜን ሱዳንና በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።በተለይም የኢትዮጵያ ነዳጅ የዋጋ ጭማሪ በማሳየት ምናልባትም አሁን የሚታየውን የኑሮ ውድነት ይበልጥ ሊያባብሰው እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አለ።

ደቡብ ሱዳን  ነጻነቱዋን ባገኘች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሱዳን ጋር ወደ ጦርነት የሚወስዳትን እርምጃ የተከተለችው በምእራባዊያን ግፊት ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት እየተሰማ ነው።