አብዲ ዒሌ ፍርድ ቤት ቀረቡ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 23/2010)ባለፈው ሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ዑመር አብዲ ዒሌ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

እሳቸውን ጨምሮ አራት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ከፍተኛ ባልስልጣናት ዛሬ ልደታ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አቶ አብዲ ዒሌ የጤና ችግር ስለገጠመኝ ጉዳዬን ውጭ ሆኜ ልከታተል ሲሉ የዋስትና መብት መጠየቃቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል የቀድሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ተወልደ በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ለ10 ዓመታት የክልሉ ፈላጭ ቆራጭ ነበሩ። ከህወሀት በኩል በሚያገኙት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ድጋፍ ታግዘው የሚቀናቀኗቸውን በሙሉ እስር ቤት እያስገቡ ራሳቸው ጭምር ድብደባ በመፈጸም ብዙዎችን ያሰቃዩ፡ ያስገደሉ ሰው ናቸው። አብዲ መሀመድ ኡመር አብዲ ዒሌ።

ጄይል ኦጋዴን በተሰኘው ጂጂጋ አቅራቢያ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በህይወት ገብተው በሞት አስክሬናቸው የሚወጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበር የሚጠቅሱት የኢሳት ምንጮች ክልሉን በከፍተኛ ጭቆና ውስጥ በመክተት መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ እንደቆዩ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟግጋቾች በየጊዜው በሚወጡ ሪፖርቶች ተመልክቷል።

እኚህ ግለሰብ ዛሬ በፍትህ እጅ ላይ ወድቀዋል። ባለፈው ቅዳሜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመልክተው።

አቶ አብዲ ዒሌ ከሌሎች ሶስት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት ጋር በአዲስ አበባ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን የዋስ መብት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አቶ አብዲ ዒሌና አብረዋቸው የቀረቡት ግለሰቦች በተለያዩ ወንጀሎች በመጠርጠራቸው ከመገለጹ ውጪ በዝርዝር የክስ ማብራሪያው አልታወቀም።

ባለፈው ሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ አቶ አብዲ ዒሌ በክልሉ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በህግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ አቃቤ ህግ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ አብዲ ዒሌ ብጤና ችግር ምክንያት ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ እንዲፈቀድላቸውና የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ የዋስትና መብት መሰጠት የለበትም የሚል መቃወሚያ በማቅረብ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም የሁለቱን ወገኖች መከራከሪያ ካደመጠ በኋላ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ይዟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አምንስቲ ኢንተናሽናል በሶማሌ ክልል በተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናትም በህግ እንዲጠየቁ በመግለጽ መግለጫ አውጥቷል።

አምንስቲ እንዳለው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን በማደራጀ፡ በማስታጠቅና ለዓመታት በክልሉና አጎራባች አከባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም ማስቆም ያልቻሉና ከጀርባ ሲደግፉ የነበሩ የፌደራል ባለሥልጣናትም በህግ መጠየቅ አለባቸው።

አምንስቲ ኢንተርናሽናል በሕግ ይጠየቁ ያላቸን የፌደራል ባለስልጣናት በስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

በሌላ በኩል የቀድሞው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ተወልደ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ እንደተመሰረተባቸው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ባለፈው ሰኔ ወር በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ቢኒያም ተወልደ ክስ የተመሰረተባቸው ከባለቤታቸውና ከቀድሞ የኢንሳ አመራሮች ጋር መሆኑ ታውቋል።