አቃቤ ሕግ የፖሊስ አመራሮች በዋስ ቢለቀቁ አልቃወምም አለ

(ኢሳት ዲሲ–ነሀሴ 7 /2010) አቃቤ ህግ የሰኔ 16ቱ ቦንብ በፈነዳበት ጊዜ ክፍተት አሳይተዋል በሚል የታሰሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የነበሩትን ግርማ ካሳን ጨምሮ 11 የፖሊስ አመራሮች በዋስ ቢለቀቁ እንደማይቃወም ገለፀ፡፡

ጉዳዩን የሚከታተለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በተያየዘ ዜና የሰኔ 16ቱን ቦንብ በማፈንዳት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ጥላሁን ጌታቸው የተባለው ግለሰብ ግን ክስ ሊመሰረትበት መሆኑ ታውቋል።

ምክትል ኮሚሽነር የነበሩትን ግርማ ካሳን ጨምሮ 11 የፖሊስ አመራሮች በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲካሄድባቸው ነበር፡፡

ሃላፊነታቸውን አልተወጡም የተባሉት እነዚሁ የፖሊስ አመራሮች የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤቱን ሲጥይቁ ቆይተዋል።እናም አቃቤ ህግ ዛሬ ላይ የዋስትና መብት ቢፈቅድላቸው አልቃወምም ሲል ተደምጧል።

በተያየዘ ዜና የሰኔ 16ቱን ቦምብ በማፈንዳት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ጥላሁን ጌታቸው የተባለው ግለሰብ ክስ ሊመሰረትበት መሆኑ ተነግሯል።

የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያመለክተው ግለሰቡ ቦምቡን ሲያፈነዳ ትከሻው ላይ ጉዳት ደርሶበታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቦምቡን በማፈንዳት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በተሽከርካሪ ጭኖ ወስዷል ፣እንዲሁም ቦምቡን ላፈነዳው ሰው የማቀበል ድርጊት ፈፅሟል በሚል የተጠረጠረው ብርሃኑ ጃፋርም ክስ ሊመሰረትበት መሆኑ ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በተጠርጣሪዎች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቆ ለአቃቢ ህግ አስረክቧል።

አቃቢ ህግም ክስ ለመመስረት ለፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ጠይቋል።

እነዚሁም ተጠርጣሪዎች  የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

ግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ክስ ለመመስረቻ ለዓቃቢ ህግ ሰባት ቀን ፈቅዷል።