አርበኞች ግንቦት7 አመጽ ነክ እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠቡን አስታወቀ

አርበኞች ግንቦት7 አመጽ ነክ እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠቡን አስታወቀ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ/ም) ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ከሰኔ 15 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ አርበኞች ግንቦት 7 “በማናቸውም መልኩ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች ምንም አይነት አመጽ ነክ እንቅስቃሴ ከማድረግ ታቅቧል” ብሎአል። “ኢትዮጵያ ዉስጥ በየትኛዉም አካባቢ የሚገኙ የነጻነት ታጋዮቻችን ከማናቸውም የአመጽ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ድርጅታዊ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል” ያለው ድርጅቱ ውሳኔው “በኢህአደግ ውስጥ ያሉ ቀልባሽ ሀይሎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለበትን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የሚያደርጉትን የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎች ለማምከን የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ጥንቃቄ ግምት ውስጥ ያስገባና ፤ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ገጽታውን ይዞ እንዲሄድ ለማበረታታት የታለመ በራስ ተነሳሽነት የተወሰደ ውሳኔ ነው።” ሲል ምክንያቱን አስፍሯል።
ድርጅቱ “ኢህአደግ ውስጥ የተነሳውና በጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ሃይል እየወሰደ ባለው እጅግ አበረታች እንቅስቃሴ የሃገራችንን ፖለቲካ ከአመጽ ነጻ በሆነ ሰላማዊ እና ስልጡን ፖለቲካ ከግብ ማድረስ እንደሚቻል ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑንም” አክሎ ገልጿል።
በውሳኔው ዙሪያ የድርጅቱን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበበ ቦጋለን አነጋገርናቸዋል። አቶ አበበ አሁን የተወሰደው እርምጃ ከአመጽ መታቀብን እንጅ ሰራዊት መበተንን የማያመለክት መሆኑን ተናግረዋል