አርበኞች ግንቦት ሰባት አቀባበል ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 8/2010) አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ወደ ሀገር ቤት በሚገባበት ሁኔታ ላይ የአቀባበል ኮሚቴው ዛሬ መግለጫ ሰጠ።

ኮሚቴው ከዛሬ ጀምሮ የአቀባበል መርሃግብሩን የተመለከቱ ስራዎችን በይፋ መጀመሩን አስታውቋል።

ናፍቆት የሚል መጠሪያ የተሰጠው የአቀባበል ስነስርዓት ላይ ኢትዮጵያውያን በመሳተፍ ለንቅናቄው መሪዎችና አባላት ደማቅ አቀባበል እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።

በሌላ በኩል በእስር የሚገኙና በአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ስም የተከሰሱ 53 ሰዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በአሜሪካ ኢትዮጵያውያን ለማነጋገር በመጡ ጌዜ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮችንም ማነጋገራቸው የሚታወስ ነው። በሁለቱ ወገኖች በተደረሰ ስምምነት መሰረት የንቅናቄ አመራሮች ወደ ሀገር ቤት በመግባት ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ መግለጫ ሰጥተዋል። በአንድ ወር ውስጥ ዝግጅታችንን አጠናቀን ወደ ሀገር ቤት እንገባለን ያሉት አመራሮች ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብረን ለውጡን ከዳር እናደርሳለን ማለታቸው መዘገቡም ይታወሳል። ዛሬ በሀገር ቤት የተቋቋመው የንቅናቄውን አመራሮች የሚቀበል አስተባባሪ ኮሚቴ መግለጫ ሰጥቷል። ኮሜቴው የአቀባበል ፕሮግራሙን ናፍቆት በሚል ስያሜ እንደሚጠራ አስታውቋል። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የአቀባበል ኮሚቴ አባላት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮችንና አባላትን ለመቀበል መላው የዲሞክራሲና ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አድርገዋል።

ከሀገር ውጪ የሚገኙ የንቅናቄው አመራሮችና አባላት ወደሚናፍቁት አገራቸውና ሕዝብ እና ወደሚናፍቁት የትግል ስልት ለመመለስ የቀራቸው ጊዜ በሳምንታት የሚቆጠር ብቻ ነው ያለው ኮሚቴው ከዛሬ ጀመሮ የአቀባበል ኮሚቴው በይፋ  ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል። የንቅናቄውን አመራሮችና አባላትን ለመቀበል የተቋቋመው ኮሚቴ ከዛሬ ጀምሮ የአቀባበል ሥነ ስርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ ድረስ የሚኖሩ የአቀባበል ተግባራትን እንዲያስተባበር ኃላፊነት እንደተሰጠውም ገልጿል። ኮሜቴው የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮችና አባላት ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ የሚኖረው አቀባበል የደመቀ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

አመራሮቹንና አባላትን ለመቀበል በተለያዩ መንገዶች ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ከኮሚቴው ጋር በመገናኘት የተቀናጀ ተግባር እንዲፈፀም አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ኮሚቴው ጠይቋል። የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በዕለቱ በተለመደው ሰላም ወዳድነቱና የዴሞክራሲ አጋርነቱ መሠረት በአቀባበሉ ላይ በመገኘት ለዲሞክራሲ ታጋዮች ያለውን ክብር እንዲገልፅ በትህትና እንጠይቃለን ሲል ኮሜቴው ጥሪ አድርጓል። የንቅናቄው አመራሮችና አባላት ወደ  ሀገር ቤት የሚገቡበት ቀን በቅርቡ እንደሚገልጽም አስታውቋል። በተያያዘ ዜና በእስር ላይ የነበሩ ከ50 በላይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አባላት መለቀቃቸው ታውቋል። በቂሊንጦ ማራሚያ ቤት የነበሩት እነዚህ እስረኞች መንግስት በቅርቡ ባወጣው የምህረት አዋጅ መስረት ከእስር ተለቀው ከቤተሰባቸው ጋር መቀላቀላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።