አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አይወክሉንም ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ደቡብ ሱዳናውያን ተቃውሞ አሰሙ

ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “በኢትዮጵያ -የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሚስተር  አሮፕ ዴንግ ኩኦል እኛን አይወክሉንም” ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ደቡብ ሱዳናውያን  ተቃውሞ አሰሙ።

ደቡብ ሱዳናውያኑ የአምባሳደር አሮፕን ሹመት የማይቀበሉት  ከአገራቸው ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ብቻ ሳይሆን፤የቪየና ኮንቬንሽን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ስምምነትን የጣሰ በመሆኑም ጭምር በመሆኑ ነው ማለታቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።

የአምባሳደሩ ሹመት የቪየናን ኮንቬንሽን እንደሚጥስ ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል፤ሰውየው ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ናቸው  እንዲሁም የኢትዮጵያ ፓስፖርት አላቸው የሚሉት ይገኙበታል።

ስለዚህም የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ከመሆናቸው በፊት ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ማንሳት እንዳለባቸው የተናገሩት ደቡብ ሱዳናውያኑ፤ በ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ የንግድ እንቅስቃሴም ስለሚያካሂዱ የፍላጎት ተቃርኖ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

አምባሳደር አሮፕ አዲስ አበባ ውስጥ ሦስት መኖሪያ ቤቶች፣አራት የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች፣ሦስት ካፊቴሪያዎች፣አስር ሚኒባሶች፣ሁለት ሆቴሎች እና ሁለት ሱፐር ማርኬቶች እንዳላቸው ሱዳን ትሪቢዩን አስነብቧል።

ከዚህም ባሻገር ደቡብ ሱዳናውያኑ፦”ላለፉት ሰባት ዓመታት በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ቆይታ ከኮሚኒቲያችን ጋር መልካም ግንኙነት የሌለውን ግለሰብ አምባሳደር አድርጎ መሾም እጅግ አሳዛኝ ነው”ሲሉ በመንግስታቸው አሠራር ላይ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide