አለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ሰጠ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 21/2011) አለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍና ብድር አጸደቀ።

ከገንዘቡ መካከል 6 መቶ ሚሊየኑ ብድር ሆኖ ቀሪው ደግሞ እርዳታ መሆኑ ተነግሯል።

ድጋፉና ብድሩ የጸደቀው የባንኩ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ባካሄደው ስብሰባ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።

የአለም ባንክ እንዳስታወቀው ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍና ብድር አጽድቋል።

ከዚሁም ውስጥ 6መቶ ሚሊየን ዶላሩ ድጋፍ ሲሆን፥ ቀሪው ግማሹ 600 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ብድር ነው ተብሏል።

ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ኢትዮጵያ  ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ  የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደረጋቸው ባንኩ አስታወሷል።

በለውጥ የመጣው የኢትዮጵያ አስተዳደር የፖለቲካ ምህደሩን ማስፋቱ ቀጠናዊ መረጋጋት እንዲመጣ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑንም ባንኩ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻዎች ማድረጉን እና ይህ ጥረቱም እንዲሳካ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ለዚህ ጥሪ የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ባንኩ አመልክቷል።

ባንኩ እንዳስታወቀው የገንዘብ ድጋፉና ብድሩ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፏን እና የኢንቨስትመንት ምህዳሯን ለማሻሻል የሚውል ነው።