ንግስት ሳባ የወርቅ ማዕድን የማምረቻ ስፍራ መገኘቱን የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ገለፁ

 

የካቲት 6 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የብሪታኒያ የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች የንግስት ሳባ የወርቅ ማዕድን ማምረቻ የነበረዉን ስፍራ ማግኘታቸዉን የተለያዩ የእንግሊዝ ጋዜጦች ገለፁ።

ከ3 ሺህ አመታት በፊት ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ወርቅ፤ የከበሩ ድንጋዮች፤ እጣን ከርቤና ቅመማ ቅመሞች ገፀ በረከት በመያዝ እስራኤልን የጎበኘችዉና ከንጉስ ሰሎሞን ቀዳማዊ ምኒልክን በመፀነስ እንደተመለሰች የምትታወቀዉ  ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ የወርቅ ማዕድን ማምረቻ ስፍራ መገኘቱን የገለፁት ዘ ጋርዲያንና፤ ዴይሊ ኔሽን የተባሉት ጋዜጦች ናቸዉ።  

በሰሜን ኢትዮጵያ ገራልታ ኮረብታማ አካባቢ የተገኘዉ ይኸዉ የወርቅ ማእድን የማዉጫ ስፍራ፤ መግቢያ 20 ጫማ በሚሆን በላዩ ላይ የፀሃይና የጨረቃ ምስል በተቀረፀበት ጥርብ ድንጋይ የተሸፈነ እንደሆነ የከርሰ ምድር ቁፋሮዉ የቡድን መሪ ሉዊዚ ሾፊልድ ገልፀዋል።

ከኮረብታማዉ ስፍራ አራት ጫማ ወደ ዉስጥ ከዘለቀዉና መግቢያዉን ከሸፈነዉ የድንጋይ ጥርብ በታች በሳባዉያን ቋንቋ የተቀረፀ ፅሁፍ፤ እንዲሁም ዘመናት ያስቆጠረ የሰዉ ራስ ቅል ተገኝቷል።  

 የብሪታኒያ ሙዚየም ባልደረባ የነበሩት ሉዊዚ ሾፊልድ ከዚህ ቀደም ከኤፍራጠስ ወንዝ ጋር የተገናኘ የጎርፍ አደጋን ለመታደግ ዙግማ በተባለች የሮማ ከተማ የከርሰ ምድር ቁፋሮ አካሂደዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢ ልማት፤ በመስኖ፤ በእርሻና ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆነ የቱሪዝም ፕሮጀክት የሚያካሄድ ግብረ ሰናይ ድርጅት በመመስረት ከትግራይ ትረስት ጋር በመስራት ላይ ይገኛሉ።

የወርቅ ማምረቻ ስፍራዉ ዉስጥ ለዉስጥ የሚያስኬድና ስፋት ያለዉ ለመሆኑ በባሉያዎች የተጠቆሙ መሆኑን የገለፁት ሾፊልድ፤ መጠኑን በሚገባ ከተረዱና በቂ ገንዘብ ካገኙ በሁዋላ ወደ ቁፋሮዉ ስራ እንደሚገቡ ማስታወቃቸዉን ጋዜጦቹ ገልፀዋል፤