ቴዎድሮስ ካሳሁን ኮንሰርት ለማዘጋጀት የመንግስትን ፈቃድ እየጠበቀ ነው

( ኢሳት ዜና – ሃምሌ 3 , 2009 )  ታውቂው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በሚሊንየም አዳራሽ በአዲስ አመት ኮንሰርት ለማሳየት ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ፈቃድ ማስታውቂያ ክፍል ጥያቄ ቢያቀርብም ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረን ምላሽ እንሰጥሃለን መባሉ ተዘገበ ።

ቴዎድሮስ ካሳሁን ጷጉሜ 5 , 2009 አ.ም ለአዲስ አመት ዋዜማ የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማቅረብ ውል መዋዋሉን የድምጻዊው ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ገልጸዋል ። ኮንሰርቱን ለማካሄድ የተስማማው አልበሙን ያከፋፈለው ኩባንያ ጆይ ኢቨንትና ፕሮሞሽን ኩባንያና ኤፕላስ ኢቨንትና ፕሮሞሽን ጋር በጥምረት ነው ። ጆይ ኢቨንት የሚሊንየም አዳራሽን ከሚያስተዳድረው አዲስ ፓርክ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው የኮንሰርት ጥያቄ መቅረቡን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል ። ነገር ግን ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረን ምላሽ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል ። በሃገሪቱ ያለው ህገ-መንግስት ግን እንዲህ አይነት ዝግጅትም ሆነ ስብሰባ እንዲሁም ሰላምዊ ሰልፍ ለማድረግ ከ48 ሰአት በፊት ቀድሞ ማሳወቅ እንጂ ፈቃድ መጠየቅን አይጠይቅም ። ምላሽም መስጠት አያስፈልገውም ።

ቴዲ አፍሮ ለኮንሰርቱ 1.8 ሚሊዮን ብር እንደሚከፈለውና ለሚሊንየም ኣዳራሽ ስራው ደሞ 1.2 ሚሊዮን እንደሚከፈል ለማወቅ ተችሏል ።ቴዎድሮስ ካሳሁን ‘’ ኢትዮጵያ ‘’ የሚለው አልበሙ ከተለቀቀ በኋላ የአዲስ አበባውን ኮንሰርት አካሂዶ በሃዋሳ በጎንደርና በመቀሌ ተጨማሪ ኮንሰርቶች ለማዘጋጀት ከስምምነት ላይ መደረሱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል ።