ተላልፈው የተሰጡት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ከፍተኛ አመራርን በተመለከተ የሶማሊያ ፓርላማ መርማሪ ቡድን አቋቋመ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 10/2010) ሶማሊያ ውስጥ ታፍነው ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው የተሰጡት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ከፍተኛ አመራርን በተመለከተ የሶማሊያ ፓርላማ መርማሪ ቡድን አቋቋመ።
ድርጊቱ የተፈጸመው የብዙዎቹ የሶማሊያ ፓርላማ አባላት ለሃይማኖታዊ ጉዳይ ሳውዲ አረቢያ በነበሩበት ወቅት እንደሆነም ተመልክቷል።

 

የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር/ኦብነግ ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑት አቶ አብዲካሪን ሼህ ሙሴ ከወር በፊት በነሀሴ 2009 በደቡብ ሶማሊያ የወደብ ከተማ ኪስማዩ ላይ በሶማሊያ ታጣቂዎች ተይዘው ሞቃዲሾ መወሰዳቸው ይታወሳል።

በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ይሁንታም የሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎች ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፈው እንዲሰጧቸው መደረጉን ኦብነግ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ይህ ርምጃ በሶማሊያ መንግስት ላይ ከየአቅጣጫው ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን ይህም ተቃውሞ ከውስጥ ጭምር የመነጨ በመሆኑ የሶማሊያ ፓርላማ በጉዳዩ ላይ በመምከር መርማሪ ቡድን ማቋቋሙን ይፋ አድርጓል።

ከሶማሊያ አፈጉባኤ ቢሮ መስከረም 8/2009 የወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው አቶ አብዲካሪን ሼህ ሙሴ እንዴት እንደተያዙና ተላልፈው የተሰጡበትን ሂደት የሚመረምር 15 አባላት ያሉት ኮሚቴ ከሶማሊያ የፓርላማ አባላት ተሰይሟል።

የተመረጡት የፓርላማ አባላት ዝርዝርም በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ሆኗል።