ቢቢሲ ኢሳትን በተመለከተ የሰራጨውን የተሳሳተ ዘገባ አረመ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 28/2011)የእንግሊዙ የዜና ማሰራጫ ቢቢሲ ኢሳትን በተመለከተ የሰራጨውን የተሳሳተ ዘገባ ማረሙን ለኢሳት በጻፈው ደብዳቤ ገለጸ።

የቢቢሲ አለም አቀፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄሚ አንገስ ኢሳት ለጻፈው የቅሬታ ደብዳቤ ትናንት በላኩት ምላሽ ቢቢሲ ባለፈው ወር ባሰራጨው ዘጋባ ኢሳት ሆን ብሎ የዘር ግጭት የሚጭር ቪድዮ አዘጋጅቶ አሰራጭቷል በሚል በቢሲ ያቀረበው ዘገባ ያስተላለፈው መልዕክት ትክክል አለመሆኑን በመገንዘብ ማስተካከያ መደረጉን በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በእንግሊዝኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቢቢሲ ያቀረበውን ዘገባ ማስተካከሉን አስታውቀዋል።

በማስተካከያውም የተባለው ቪድዮ የተዘጋጀው በሌላ አካላት እንደነበርና ኢሳት ወዲያውኑ ቪድዮውን ማውረዱንና ይቅርታ መጠየቁን በቢሲ በማስተካከያው ላይ ጨምሯል።

ዳይሬክተሩ ቢቢሲ ማስተካከያ ለማድረግ በመዘግየቱ ይቅርታ ጠይቀው በዚሁ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ተሰራ ያሉትን የተሳሳተ ዘገባ ኢሳትን ለመጉዳት ያለመ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።