በጎንደርና ባህርዳር ሁለት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በሶስት አመት ይጠናቀቃል

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት11/2011)በአማራ ክልል ጎንደርና ባህርዳር ሁለት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በ1መቶ ሚሊየን ብር ለመገንባት የሚንቀሳቀሰው ወንፈል ተራድኦ ተቋማቱን በሶስት አመታት ውስጥ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል ገባ።

በአሜሪካን ሃገር የተቋቋመውና በክልሉ ተወላጆች ኢትዮጵያውይን የተመሰረተው ድርጅት ግንባታውን የሚያከናውነው ከአማራ ልማት ማህበር ከዩኒቨርስቲዎች ጥምረት ፎረምና ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ነው።

የወንፈል ተራድኦ ስራ አስፈጻሚ አባላት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ለግንባታው ከሚውለው 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ውስጥ ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆነውን ድርጅታቸው ይሸፍናል።

በአማራ ክልል የትምህርት ተደራሽነትና የጥራት ችግር ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የስታስቲካል መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በክልሉ እ.ኤ.አ በ2017/18 ለ1ኛ ደረጃ ትምህርት እድሚያቸው ከደረሰ ታዳጊ ልጆች 20 በመቶ የሚሆኑት እድሉን አላገኙም።

ትምህርት ቤት ከገቡት ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያቋርጣሉ።

በጉዳዩ ላይ ጥናት በተደረገበት መረጃ መሰረት ለከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት የሚበቁት 19 በመቶ ብቻ ናቸው።

ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በአማራ ክልል ለከፍተኛ ትምህርት ወይንም ዩንቨርስቲ የሚገቡት 5 በመቶ ብቻ መሆናቸው ነው የተገለጸው።

ይህንን አሳሳቢ ችግር የተገነዘቡት በሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የክልሉ ተወላጆች ወንፈል ተራድኦ በሚል ባቋቋሙት ምግባረ ሰናይ ድርጅት በጎንደርና በባህርዳር ሁለት አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

የወንፈል ተራድኦ ድርጅት የስራ አስፈጻሚ አባላት በዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ድርጅታቸው በትምህርት ብቻ ሳይሆን በጤና አገልግሎት ነጻ የትምህርት እድል በመስጠትና በአካባቢ ጥበቃ ለመስራት ራዕይ ሰንቀው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።

የወንፈል ተራድኦ ሊቀመንበር እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነህ አበበ እንደገለጹት ለግንባታው ከሚያስፈልገው ወጭ 1/3ኛ ያህሉ በድርጅታቸው ይሸፈናል።

ይህም ከ3 የተለያዩ አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ ነው ብለዋል።

የተሰጠንን እንሰጣለን በሚል መሪ ቃል ለስኬት ያበቃቸውን ማህበረሰብ ለመርዳት መንቀሳቀስ የጀመሩት የወንፈል ተራድኦ አመራሮች ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗ ይህንን በጎ ስራ ለመስራት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።

ወደ ትምህርት ቤት ግንባታ የገቡትም በልጅነታቸው የገጠማቸውን ችግር በማስታወስ ጭምር መሆኑን ዶክተር ይንገስ ይግዛው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ጎንደርና ባህርዳር የሚገነቡት ትምህርት ቤቶች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ገንዘቡ ከተሰበሰበ በኋላ በ3 ዓመታት ውስጥ ፕሮጀክቱን ለማንቀሳቀስ ታቅዷል።

እናም ይህንን እቅድ በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም የክልሉ ተወላጆች ድጋፋቸውን እንዲሰጡ የወንፈል ተራድኦ አመራሮች ጥሪ አቅርበዋል።