በጋሞጎፋ ዞን ከማዳበሪያ እዳ ጋር በተያያዘ 7 ሰዎች ራሳቸውን አጠፉ

የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአርባ ምንጭ ዘጋቢያችን እንደገለጠው በአለፉት 2 ወራት ብቻ ከማዳበሪያ እዳ ጋር በተያያዘ 7 አርሶአደሮች  ራሳቸውን ሰቅለው፣ ወደ ገደል ወርውረው ወይም በአካባቢ ምልሺያ በደረሰባቸው ድብደባ ሞተዋል።

በ1997 ዓም ያራ የተባለው ተራድኦ ድርጅት አቶ መለስ ዜናዊ በአገራቸው ላካሄዱት የአረንጓዴ አብዮት  እንቅስቃሴ እውቅና ለመስጠት በሚል  200 ሺ ዶላር ሸልማት መስጠቱ ይታወቃል።

በጊዜው የኖርዌይ አፍተን ፖስተን የተባለው ጋዜጣ  ሸላሚው ድርጅት ለኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት ማዳበሪያ ሲያቀርብ የነበረ መሆኑን ሽልማቱም እንደ መደለያ እንደሚቆጠር አጋልጧል።

ጉዳዩም ለአቶ መለስ ዜናዊ የተሰጠ ጉቦ ነው በሚል ሰፊ አለማቀፋዊ ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር። አቶ መለስም ተቃውሞው የሚያስከትለውን ተጽእኖ በመፍራት ገንዘቡን ለአንድ የሴቶች ድርጅት ማስረከባቸውን ገለጡ።

የአርባ ምንጭ ዘጋቢያችን እንደሚለው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማዳበሪያ የኢህአዴግ ድርጅት በሆነው አምባሰል ኩባንያ በኩል የአቶ መለስ ዜናዊ ሸላሚ ከሆነው ያራ ፋውንዴሽን  በገፍ አስገብቷል።

በደቡብ የሚገኙ አርሶአደሮች ማዳበሪያው ለአካባቢያችን ተስማሚ ይሁን አይሁን ሳናውቅ ማዳበሪያውን አንወስድም በሚል ሲከራከሩ ቢቆዩም፣ የመንግስት ባለስልጣናት ማዳበሪያውን በግድ እንዲወስዱ እና ገበሬዎቹ ቀስ ብለው እንዲከፍሉ  በማግባባት ገበሬዎቹ ማዳበሪያ በብዛት እንዲወስዱና አምባሰልን ከኪሳራ እንዲታደጉት ለማድረግ ሞክረዋል።

ይሁን እንጅ አርሶአደሮች ማዳበሪያውን ተጠቅመው ሁሌም ከሚያመርቱት ምርት የተለየ ምርት ለማምረት ባለመቻላቸው፣ የማዳበሪያውን እዳ ለመክፈል አልቻሉም። የዞኑ ባለስልጣናትም ባለፉት 2 ወራት ወደ ገጠር በመውረድ ገበሬው የማዳበሪያ እዳውን በሀይል እንዲከፍል ሲያስገድዱት ቆይተዋል።

ኢሳት በቅርቡ እንደዘገበው በአንዳንድ ወረዳዎች ህዝቡ የተወሰኑ ባለስልጣናትን በመግደል እና የመኪና መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሞውን ሲገልጥ ቆይቷል። የወረዳው ባለስልጣናት ግን ከፌደራል መንግስት የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራት በአርሶአደሩ ላይ የሚያደርሱትን ተጽኖ አሁንም አልቀነሱም።

 ሶስት አርሶአደሮች የቤተሰቦቻችንን ስቃይ አናይም በማለት ራሳቸውን በገመድ አንቀው ሲገድሉ፣ አንዱ ደግሞ ራሱን ገደል ውስጥ ውርውሮ አጥፍቷል። 3 ሰዎች ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው ማለፉን ዘጋቢያችን ተጨባጭ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ዘግቧል።

አንዳንድ የክልሉን ባለስልጣናትም ” ችግሩ ከሀቅማቸው በላይ መሆኑን እና የፌደራል መንግስት የፖሊሲ ለውጥ ካላደረገ በስተቀር በክልሉ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ እንደሚሄድ ” ለዘጋቢያችን  ገልጠዋል።

የየራ ፋውንዴሽን ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሸጠው ማዳበሪያ ለበርካታ አርሶአደሮች ሞት ምክንያት ሆኗል ሲሉ አንድ የአንድነት ፓርቲ የደቡብ ተወካይ ገልጠዋል።

የኢህአዴግ ንብረት የሆነው አምባሳል ኩባንያ አርሶአደሩን በማዳበሪያ እና በምርጥ ዘር እዳ አስሮ በመያዝ ባርያ እንዳደረገውም አክለዋል።

ውድ ተመልካቾቻችን በደቡብ ክልል ከማዳበሪያ እና ከሌሎች የመልካም አስተዳዳር እጦት ጋር በተያያዘ የሚነሱትን ችግሮች በተመለከተ ከአንድ የአካባቢው ተወላጅና ፖለቲከኛ ጋር በቅርቡ ውይይት የምናደርግ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጣለን።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide