በጋምቤላ ከተገደሉት ሁለት ፖሊሶች መካከል አንዱ የአመራር አባል ነው

የካቲት 13 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢሳት ባለፈው ሳምንት ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላትና አንድ ሲቪል ሰራተኛ መገደላቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ባወጣው ዝርዝር ዘገባ ደግሞ የካቲት 8 ቀን ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ከተገደሉት መካከል አንደኛው የጋምቤላ ልዩ ሀይል አመራር መኮንን ሲሆን ፣ ከቆሰሉት ሲቪሎች መካከል ደግሞ  የሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ የሆነው ሳዑዲ ስታር እርሻ ልማት ኩባንያ የፋይናንስ ኃላፊ ይገኙበታል።

ግድያውን ያከናወኑት የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በአኙዋክ ንጹሃን ዜጎች ላይ  የተፈጸመው የዘር ማጥፋት አስቆጥቷቸው የሸፈቱ አማጺያን እንደሆኑ መገመቱን፣  ሟቹ የጋምቤላ ልዩ ኃይል አዛዥ ኦባንግ አማው ኡቹዶ ቀደም ሲል ከነዚሁ አማጺያን ጋር ሸፍተው የነበሩና በኋላ ግን እጃቸውን በመስጠት የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ የተቀላቀሉ የአኙዋክ ብሔረሰብ አባል ናቸው ሲል አኢጋን ገልጧል።

ባለሶስት ኮከብ ማዕረግ ያላቸው ኦባንግ አማው፣ አብረዋቸው አምጸው የነበሩትን ጓዶቻቸውን በመክዳት በ1997 ዓም እጃቸውን ሰጥተው ሲገቡ ወዲያውኑ በህወሃት/ኢህአዴግ አማጺያኑን የማጥፋት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር።

ኦባንግ አማው ህወሃት/ኢህአዴግን ሲቀላቀሉ ከተሰጣቸው ጥቅማ ጥቅም በተጨማሪ የአጭር ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ የሶስት ኮከብ ማዕረግ አግኝተዋል።

ባለፈው ሐሙስ የካቲት 8፤ 2004 ዓም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ክልሉ የሰጣቸውን ተሽከርካሪ በመያዝ ወደ ኦቦድ ኬላ በማምራት ላይ ሳሉ ፤  በድንገት የታጠቁ አማጺያን ከጫካ በመውጣት ኦባንግና ኦፒዮን መሳሪያቸውን እንዲጥሉ ቢያዙዋቸውም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እና ተኩስ ለመክፈት በሞከራቸው ተገድለዋል።

በዚህ መሃልም የሼክ ሙሀመድ አላሙዲ የሳዑዲ ስታር ንብረት የሆነች ተሽከርካሪ ብቅ ማለቱዋን፣ ኬላውን እየጠበቁ ያሉት አማጺያን ገመድ በመወጠር ተሽከርካሪዋን ለማስቆም ምልክት ቢሰጡም፣ አሽከርካሪው ግን ወዲያው ፍጥነት በመጨመር ኬላውን ጥሰው መሄዳቸውንና አማጺያኑ አከታትለው በመተኮስ ሹፌሩንና አጠገባቸው የነበሩትን ሲያቆስሏቸው ተሽከርካሪዋ እንድትቆም ማድረጋቸውን አኢጋን ገልጧል።

በወቅቱ ተሽከርካሪዋ ውስጥ የነበሩት የሳዑዲ ስታር የፋይናንስ ኃላፊ ከባንክ ገንዘብ አውጥተው እንደነበር አማጺያኑ መረጃ ሳይኖራቸው እንደማይቀር ድርጅቱ ገልጦ፣ በወቅቱ አማጺያኑ “እኛ እናንተን አንፈልግም፡፡ ጉዳያችን መሬታችንን ከሚነጥቁና ህዝባችንን እየረገጡ ከሚያሰቃዩት ኃይሎች ጋር ብቻ ነው” በማለት መናገራቸውንም አክሎአል።

“በመጨረሻም ኬላው ውስጥ የነበረውን መሳሪያና ጥይት፣ የተገደሉትን ግለሰቦች መሳሪያ ጨምረው በመሰብሰብ አማጺያኑ ተሰውረዋል፡ የቆሰሉት የሳዑዲ ስታር የፋይናንስ ኃላፊና አሽከርካሪያቸው ለህክምና ወደ ጋምቤላ ቢወሰዱም የፋይናንስ ኃላፊው በከፍተኛ ደረጃ ስለተጎዱ በነጋታው በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ በዚሁ የጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ ሸንቶዋ ከተማ የመሳሪያ ግምጃ ቤት መዘረፉን፤ ጎክ ወረዳ ፉኚዶ ከተማ የመከላከያ ማዘዣ ውስጥ ጸጉረ ልውጦች መታየታቸውን ተከትሎ ከመከላከያ ኃይል በተከፈተ የተኩስ እሩምታ በመኝታ ላይ የነበሩ ንጹሃን መገደላቸውን፣  በቅርቡ የምስጢር ደኅንነት ሹም ከፕሬዚዳንቱ ቤት ስብሰባ ጨርሰው መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ መደገላቸው በአካባቢው የነገሰውን ውጥረት አመላካች ሆኗል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide