በጉጂ ዞን የተፈናቀሉት የጌዲዮ ተወላጆች እስካሁን እርዳታ አልደረሰላቸውም

በጉጂ ዞን የተፈናቀሉት የጌዲዮ ተወላጆች እስካሁን እርዳታ አልደረሰላቸውም
(ኢሳት ዜና ግንቦት 09 ቀን 2010 ዓ/ም) ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑ የጌዲዮ ተወላጆች ከጉጂ ዞን ተፈናቅለው ገደብ ከተማ እየገቡ ቢሆንም፣ እስከዛሬ ድረስ እርዳታ አለመቅረቡን የከተማዋ ምንጮች ገልጸዋል።
ተፈናቀዮች ዛሬም ድረስ ከገጠር ወደ ከተማ እየገቡ ሲሆን፣ ብዙዎቹ እርዳታ በማጣታቸው ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ልመና ተሰማርተዋል። ሁኔታው እጅግ አስከፊ ነው የሚሉት የከተማዋ ምንጮች፣ አፋጣኝ እርዳታ ካልተደረገ በስተቀር ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
በቅርቡ በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ከ100 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ12 ሺ በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል። ካለፈው እሁድ ጀምሮ በተነሳው ግጭት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ለማወቅ የተደረገው ጥረት ግን አልተሳካም።