በደቡብ ገበሬዎች ራሳቸውን እያጠፉ አንዳንዶች ባለስልጣናትን እየገደሉ ነው

የካቲት 5 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል ፍትሃዊ ባልሆነው የማዳበሪያ ስርጭትና እዳ አከፋፈል የተማረሩ ገበሬዎች እራሳቸውን ማጥፋታቸውን ፤ አንዳንዶቹም የወረዳውን ኃላፊዎች በመግደልና ወደ አካባቢያቸው እንዳይደርሱ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ምንጮች አስታወቁ፡፡

የኢህአዴግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር አውለው የሚያከፋፍሉት ማዳበሪያ የመሬቱን ሁኔታ፣ የገበሬውን ያስተራረስ ልማድ እና የገበሬውን ማሳ ይዞታ ግምት ውስጥ ሳያስገባ በግድ የሚሰራጭና የምርት ወቅት ሲደርስም ድርጅቶቹ የገበሬውን አፍንጫ ይዘው ከገቢው በላይ እዳ የሚያሰባስቡበት መንገድ  ገበሬውን የመንግሥት ጭሰኛ ለማድረግ እየተጠቀሙበት ነው በማለት የአካባቢው ነዋሪዎች ለዘጋቢያችን ገልጠዋል።

በዚህ የተነሳም ሰሞኑን የመንግሥት ካድሬዎች የማዳበሪያ እዳ ለመሰብሰብ ገበሬውን በማስጨነቃቸው ለአንዳንድ ገበሬዎች ራስን ማጥፋት ምክንያት እየሆነ ሲሆን፣  በሁኔታው የተማረሩና በገዢው ፓርቲ ተስፋ የቆረጡ ገበሬዎችም የመስተዳድር አመራሮችን መግደል ጀምረዋል ፡፡

ለዚህ ከስተት ምክንያቱ ሁለት ነው ያሉት አንድ የደቡብ ክልል የግብርና ባለሙያ አንደኛ የመንግሥት ካድሬዎች ለኢህአዴግ ድርጅቶች ቢዝነስ ሲባል ገበሬውን በግድ ማዳበሪያ እንዲወስድ ማድረጋቸው ሲሆን ፣ ሁለተኛ ደግሞ የእዳው አመላለስ ስርዓትን የተከተለ አለመሆኑና ለፖለቲካ ፍጆታ ጥቅም ሲባል ገበሬውን አስጨንቀው መያዛቸው ነው።

ካድሬዎቹ  እዳ የሚያስመልሱት ሆን ብለው በጉልበት፣ በጡንቻና በመሳሪያ ታጣቂ ፖሊስ መሆኑ ለችግሩ መከሰት ዋና ምክንያት ሆኗል።

በጋሞ ጎፋ ዞን  በቁጫ ወረዳ አርሶ አደር ጥላሁን ጤራ ባቦ የተባለ ገበሬ የኢህአዴግ ካድሬዎች በማዳበሪያ እዳ ሳቢያ ለሁለት ቀናት አስረው ሲያስጨንቁትና እዳውን በአስቸኳይ ካልከፈለ መሬቱን እንደሚነጥቁትና እንደሚያፈናቅሉት ነግረው ሲፈቱት ወዲያው ልጆቼን ይዤ የትም አልበተንም፣ አልሰደድም ብሎ ራሱን አንቆ ገድሏል፡፡

በዚህ ሳምንትም በዚሁ ወረዳ ውስጥ አንድ ገበሬ /ለጊዜው ሥሙ አልደረሰንም/ በተመሳሳይ ሁኔታ ውሃ ውስጥ (ወንዝ) ገብቶ ራሱን አጥፍቷል፡፡

ሰሞኑን በሁኔታው እጅግ የተበሳጩ የአካባቢው ገበሬዎች እዳ ክፈሉ እያሉ የሚመጡ የኢህአዴግ ካድሬዎችንና የወረዳ መስተዳደሮችን መግደል ጀምረዋል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን ዑባ ማሌ ዘባ ቀበሌ ሊቀመንበርና ጸሐፊው እዳ ሊያስከፍሉ ሲመጡ በአካባቢው ገበሬዎች ተደብድበው የተገደሉ ሲሆን፣  በኡባ ማሌ ወረዳ ያላ ቀበሌ ውስጥ ደግሞ የወረዳው የሚሊሺያ አዛዥ በአካባቢው ነዋሪዎች በተመሳሳይ መንገድ ተገድለዋል ፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን በከሜላ ዛላ ዑባ ማሌ ወረዳ ደግሞ ሰሞኑን አንድ የመንግሥት ፖሊስ በመገደሉ መንግሥት በግልጽ ህዝቡን ማስጨነቅና ማስፈራራት ጀምሯል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በጎፋ አካባቢ የገዜ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች ማንኛውም የካቢኔ አባላት ወደ ቀበሌዎች ውስጥ እንዳይገቡ ወደ ጃውላና ባጋባርዛ የሚሄደውን መንገድ በእንጨት ግንድና አጠና በመዝጋት “ማዳበሪያ በፍላጎት እንጂ በግድ አይሰጠን፣ መሬታችን ለም ነው፣ ገንዘብ የለንም፣ እዳ አትቆልሉብን” በማለት የመንግስትን የሥራ እንቅስቃሴ አስተጓጉለዋል።

በደቡብ ክልል በየጊዜው የሚታየው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ያሰጋው መንግስት የፌደራል ፖሊሶችን በአካባቢው በብዛት ማሰማራቱን ለማወቅ ተችሎአል።

ጥር 21 ቀን የአስተርዮ ማርያም በሚከበርበት እለት በቁጫ ወረዳ አንድ ፖሊስ በህዝብ ላይ ከተኮሰ በሁዋላ፣ በአካባቢው የተሰማራው የፌደራል ፖሊስ አሁንም ቅኝት እያደረገ ነው።