በደቡብ ክልል በዳውሮ ዞን የዋካ ከተማና አካባቢው ህዝብ ከመብት ጥያቄዎች ጋር ያነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከ90 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ተሰማ ችግሩ ግን አሁንም አልበረደም

ኢሳት ዜና:-ከሳምንት በፊት  በዋካ ከተማ ከወረዳና ከልማት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናት ችግሩን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ከመሞከር  ይልቅ የሀይል አማራጭ ተጠቅመዋል። በዚህም የተነሳ በየቀበሌው የሚገኙ ወጣቶች መንግስትን ለመገልበጥ አስባችሁዋል እየተባሉ ከእየቤታቸው እየተወሰዱ በመታሰር ላይ ናቸው። በርካታ ወጣቶችም እስሩን በመሸሽ አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ ነው። መመህራን እና ተማሪዎች ባደረጉት ስብሰባ ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት የወሰዱትን እርምጃ አውግዘዋል። ተማሪዎቹና መምህራኑ የመብት ጥያቄዎች በሀይል ሊጨፈለቁ እንደማይገባና የመንግስት ባለስልጣናት በህዝቡ ላይ የሚወስዱት የእስር  እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

በወረዳው ያለው ውጥረት አሁንም እንዳለ ሲሆን ልዩ ሀይል 24 ሰአት ሙሉ አካባቢውን እየተቆጣጠረው እንደሚገኝ የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።  ህዝቡ መንግስት ችግራችንን የማይፈታለን ከሆነ ግብር አንከፍልም ማለት መጀመሩንም ሰዎቹ አክለው ተናግረዋል። የኢሳት ዘጋቢ በአካባቢው የሚፈጸመው እርምጃ ስጋት ላይ ስለጣለው አካባቢውን በመልቀቅ መሄዱን ገልጦ፣ በአሁኑ ጊዜ በከተማው ስላለው ሁኔታ ተጨባጭ መረጃ ለማቅረብ አለመቻሉን ገልጧል። ይሁን እንጅ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም በወረዳው ከፍተኛ የሆነ ውጥረት መስፈኑን እየተናገሩ ነው።

በእስር ላይ የሚገኙትን የአካባቢ ሽማግሌዎች ተክተው አዲስ የተመረጡት ሽማግሌዎች ደግሞ ወደ አዋሳ በመሄድ ለክልሉ ባለስልጣናት አቤት እያሉ ነው። ቁጥራቸው 20 የሚደርስ የአገር ሽማግሌዎች ወደ አዋሳ የተጓዙት ፍትህ ጠፋ፣ በደል ደረሰብን በማለት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል። ተቃውሞውን ከሚያስተባብሩት ሰዎች መካከል አንድ ወጣት ለኢሳት እንደገለጠው የመንግስት ባለስልጣናት አንዳንድ ነዋሪዎችን በገንዘብ በመደለል ያነሳነው ጥያቄ የእኛ ሳይሆን የጸረ ሰለም ሀይሎች ነው እያሉ እንዲፈርሙ እያደረጉዋቸው ነው።

በአሁኑ ጊዜ በርካታ የኢህአዴግ ካድሬዎች ለሰዎች ገንዘብ በመስጠት ፊርማ እያሰባሰቡ መሆኑን አስተባባሪው ገልጧል። በሌላ በኩል ደግሞ ቶጫ የሚባለው ወረዳ በዋካ የተነሳውን ተቃውሞ እንደሚደግፍ በይፋ በመግለጡ የመንግስት ታጣቂዎች ወደ ስፍራው ማምራታቸው ታውቋል። የዋካ ህዝብ የጠየቀው የመብት ጥያቄ ተገቢ ነው ማለት የጀመሩት የቶጫ ወረዳ ነዋሪዎቸ እኛም ልማት እንፈልጋለን እያሉ እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል።

የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን እስካሁን ድረስ በዋካ ስለተነሳው ተቃውሞ ዘገባ አላቀረቡም፣ መንግስትም ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም። ባለፈው ሳምንት ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ማህበራዊ አግልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በሙሉ ተዘግተው የነበረ ሲሆን በዛሬው እለት አንዳንድ ሱቆች መከፈታቸው ታውቋል። ተማሪዎች ግን ወጣ ገባ ከማለት በቀር በይፋ ትምህርት አልጀመሩም። ወጣቶቹ   ” ዳውሮ ላይ የመንግስት ስርአት የለም፣ ልማት የለም፣ እስራትና ድብደባ ይቁም፣ የሚሉ መፈክሮችንና “ነጻነት አጣን እኛ የዋካ ልጆች፣ ስርአቱ ገደለን የዋካን ልጆች” የሚል ይዘት  ያለው መዝሙር ሲዘምሩ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።