በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የነብሮ ገዳዮችና አስገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ በተቃውሞ ሰልፍ ጠየቁ።

በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የነብሮ ገዳዮችና አስገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ በተቃውሞ ሰልፍ ጠየቁ።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ/ም) በደቡብ አፍሪቃ ለተቸገሩ ወገኖቹ ቀድሞ በመድረስ የሚታወቀው ገዛኸኝ ገብረመሰቀል ወይም ነብሮ በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ እንደ አለኝታና መከታ የሚታይ ተወዳጅ ሰው ነው።ሜይል ኤንድ ዘጋርዲያን-ህልፈቱን ተከትሎ ባጠናቀረው ሰፊ ሀተታ እንዳስነበበው።
ይህ ሀገር ወዳድ የቁርጥ ቀን ልጅ የዛሬ ወር አካባቢ ነበር በቅጥረኞች የመገደሉ ዜና የተሰማው። የነብሮ ድንገተኛና አሳዛኝ ሞት በጆሀንስበርግ፣በደርባን እና በፕሪቶሪያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮያውያንን አስደንግጧል።
በርካቶች “ያረፉት ጃኮ ዙማ ናቸው? ወይስ ታቦ ምቤኪ?” ብለው እስኪጠይቁ ድረስ፣ በሥር ዓተ ቀብሩ ዕለት የሂልብሮው ጎዳናዎች አረንጓዴ ቢጫና ቅዩን ሰንደቅ በሚያውለበልቡ ኢትዮጵያውያን ተጨናንቀው ታይተዋል። ኢትዮጵያውያኑ ከየከተሞች በነቂስ በመውጣት ፍቅራቸውን እየገለጹ በለቅሶ ሸኝተውታል።
እነሆ ዛሬ ደግሞ በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በጠራዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ ኢትዮፕያውያኑ ፕሪቶሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት በመገኘት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የነብሮ አስገዳይ የሆኑ ቅጥረኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
በህይወት ሳለ የኢትዮጵያ መንግስትን ኢፍትሀዊ አሰራሮች ለመቃወም በሚጠሩ ሰልፎች ላይ ከፊት መስመር በመገኘት ለሚታወቀው ለገዛኸኝ ነብሮ ሞት አብዛኛው ኢትዮጵያውያን ተጠያቂ ያደረጉት የፕሪቶሪያውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው።
ምክንያት? ከመሞቱ አንድ ቀን በፊት ምሽት ላይ ኤምባሲው በቤል ፎድር ቪው ባለው በሄለኒክ ሲፕረስ ክለብ ከደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች ጋር በነበረው የስብሰባ ፕሮግራም ላይ ተገኝቶ ጥያቄ ለማቅረብ ቢሞክርም ስብሰባው ላይ እንዳይገኝ በመከልከሉ ከፍ ባለ ድምጽ ተቃውሞውን አሰምቶ እና ከኤምባሲው ሰዎች ጋር ኃይለቃል ተመላልሶ ወደ ቤቱ ይመለሳል።
ሜይል ኤንድ ዘጋርዲያን እንደዘገበው ገዛኸኝ የዚያን ቀን ምሽት እቤቱ እንደገባ “አርፈህ ልጆችህን ማሳደግ ካልፈለግክ የተደገሰልህን ዋጋ በቅርቡ ታገኛለህ የሚል መል ዕክት ደረሰው። በሚቀጥለው ዕለት ተገደለ።
ለዚህም ነው-ኤምባሲው ደጋግሞ ቢያስተባብልም፣ ኢትዮያውያኑ ግን መቶ በመቶ ገዛኸኝን በቅጥረኞች ያስገደለው ኤምባሲው ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የሚገልጹት።
በዛሬው የፕሪቶሪያ ሰልፍ “የገዛኸንን ደም አፍሳሾች እስከመጫው እንፋረዳቸዋለን”ሲሉ የተደመጡት ኢትዮጵያውያን፣ የነብሮህ ህይወት የነጠቁትን ዝም ማለት በራስ ላይ ሌላ አደጋ መጋበዝም ጭምር ነው ይላሉ።
ሰልፈኞቹ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ “ጀግና ነው ጀግና ነብሮ፣ነብሮ፣ ገዳይ ነው ጋዳይ ወያኔ ወያኔ”እያሉ በዝማሬ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተደምጠዋል።
በሰልፈኞቹ ከፍተኛ ሀገራዊና ወገናዊ ስሜት በተቀላቀለበት መፈክር ፍርሀት ያደረባቸው የፕሪቶሪያው ኤምባሲ ሰራተኞችም ጽህፈት ቤቱታቸውን በመዝጋት ከሰልፈኞቹ ቁጣ ለመደበቅ ሞክረዋል።
በነብሮ ላይ የተፈጸመው ግድያ ከትግላቸው አንዲት ኢንች ወደ ኋላ እንደማይመልሳቸው፣ ይልቁንም ነብሮ ቆሞለት ለነበረው ዓላማ ዕውን መሆን ይበልጥ ወገባቸውን እንዲያጠብቁ እንደሚያደርጋቸው የገለጹት፣ኢትዮጵያውያኑ ፣በነብሮ ጉዳይ ፍትሀዊ ፍርድ እስኪያገኙ ድረስ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።