በደሴ ከተማ አንድ ተጠርጣሪ ወጣትን ለመያዝ በተፈጠረ ግርግር የትራንስፖርት አገልግሎት ለሰዓታት ተቋረጠ

(ኢሳት ሐምሌ 26/2010)ነዋሪነቱ አራዳ በመባል በሚታወቀው የደሴ ከተማ ኗሪ የሆነውን ወጣት ባዬን ለመያዝ ፖሊስ የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥቶ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲሞክር ሁኔታውን በቅጡ ባልተረዱ የአካባቢው ነዋሪዎችና በፀጥታ አስከባሪዎች መሃከል ግጭት ተቀሰቀሰ።
ተጠርጣሪውን ይዘው የአዲስ አበባ ታርጋ ባላት ሲቪል መኪና ሲጓዙ በነበሩት ፖሊሶች ላይ በከተማው መውጫ ኬላ አቅራቢያ ወጣቶች ግርግር በመፍጠር የተሽከርካሪዋን መስታወት በመስበር ግለሰቡን አስመልጠዋል። የፀጥታ አስከባሪዎቹ ጉዳት ሳይደርስባቸው ማምለጣቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል።
ወጣት ታዬ የተሰረቁ ንብረቶችን ገዝቶ በመሸጥ የሚታወቅና ከዚህ በፊትም በፖሊስ እንዲያዝ የፍርድ ቤት ማዘዣ ወጥቶበታል። በመኖርያ ቤቱም የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪዎች ቲቪ፣ ሞባይል ስልኮችን ጨምሮ የተለያዩ ሁለት አይሱዙ ንብረቶችን መያዛቸው ይታወቃል።
ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም በደህንነት አካላት ታፍነው ከሚወስዱ ግለሰባች ጋር በማመሳሰል ለወንጀለኞች ከለላ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ የከተማ ነዋሪዎች አሳስበዋል። ግርግሩን ተከትሎ ወደ ከተማዋ የሚወጡና የሚገቡ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎች ለሰዓታት ለመቆም ተገደዋል። ተጠርጣሪውን ለመያዝ በፖሊስና በነዋሪዎቹ መሃከል ይህን ዜና እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ውጥረት መኖሩን ምንጫቻችን አስታውቀዋል።