በወልቂጤ በተነሳው ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካታ ንብረትም መውደሙን ነዋሪዎች ገለጹ

በወልቂጤ በተነሳው ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካታ ንብረትም መውደሙን ነዋሪዎች ገለጹ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ/ም) ባለፈው እሁድ የእግር ኳስ ጨዋታን ሰበብ በማድረግ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ ዛሬ ግጭቱ ተባብሶ የሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካታ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች መውደማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ትናንት ማክሰኞ ደግሞ ካምፕ 99 በሚባለው አካባቢ ከህገወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ የከተማው ሹሞች ቤቶችን ሂደው በሚያፈርሱበት ሰዓት የቀቤና ተወላጆች፣ የመዘጋጃቸው ሹሞች ጉራጌዎች ናቸው በማለት ተቃውሞ እንደጀመሩ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ዛሬ ግጭቱ በከፍተኛ ደረጃ ተባብሶ በመቀጠሉ በርካታ ቤቶችና መኪኖች ተቃጥለዋል።
በግጭቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ነዋሪዎች ህይወታቸው አልፏል። ዘርማ እየተባሉ የሚጠሩ የጉራጌ ተወላጅ ወጣቶችን ቤቶችና መኪኖችን ማቃጠላቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በድርጊቱ የተበሳጩት የጉራጌ ተወላጆች ራሳችንን እንከላከላለን በማለት ጥቃት መፈጸማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ግጭቱን የአዲሱን የዶ/ር አብይ አመራር ለመቀበል ፍላጎት ያጣው ደቡብ ክልልን የሚመራው የህወሃት ደጋፊ የሆኑ የደኢህዴን ቡድን አባላት ናቸው በማለት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።