በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልሎች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ

ሚያዚያ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልሎች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ  22 ሰዎች መሞታቸውና በርካቶች መቁሰላቸው ተዘገበ።

 እንደ ፍኖተ-ነጻነት ዘገባ በሁለቱ ክልሎች የድንበር ነዋሪዎች መካከል ለተፈጠረው ግጭት ምክንያቱ የቦታ ይገባኛል ጥያቄ ነው።

 የአካባቢው ነዋሪዎች  እንደገለጹት ከሆነ “በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ልዩ ሥፍራው “ጊዳ ኪራሞ” እና “ጊዳ አያና” በተባሉ ወረዳዎች ለተነሳው ግጭት መንስዔው፤ አቤንቱ፣ ቄሎ እና ዋስኪ በተባሉ አካባቢዎች የተፈጠረ የይገባኛል ጥያቄ ነው፡፡

 ለዘመናት ተከባብረውና ተዋደው የሚኖሩት እነዚህ ህዝቦች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ እንደዚህ ዓይነት ግጭት ውስጥ መግባታቸው፤ የአካባቢውን ነዋሪዎች እጅግ ማሳዘኑ ታውቋል።

 “ከዚህ በፊት በ2000 ዓ.ም  በ አካባቢው የተፈጠረው ተመሣሳይ ግጭት  ለ200 ሰዎች ህይወት ሞት፣ ለበርካቶች መቁሰልና መፈናቀል ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም።

 “የአሁኑን ግጭት አሣሳቢ የሚያደርገው ግን ፤በደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆችን የመንግስት ባለሥልጣኖች፦”ወደ አገራችሁ ሂዱ” በማለት ባባረሩ ማግስት የተከሰተ መሆኑ ነው”ብለዋል-አንድ የአካባቢው የአገር ሽማግሌ- ለኢሳት ዘጋቢ በሰጡት አስተያዬት።

“እየሆነና እየተሰማ ያለው ነገር ሁሉ ጆሮን የሚቀፍ ነው፤ይህ ግጭት በባህርይው ኢትዮጵያዊ አይደለም” ሲሉም አክለዋል-የአገር ሽማግሌው።

 በአሁኑ ጊዜ  የቆሰሉት በርካታ ሰዎች በለቀምት ሆስፒታል በመታከም ላይ ናቸው።

  ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ “ለዘመናት በጉርብትና በሠላም ይኖር በነበረው ሕዝብ መሀከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠረ ያለው ግጭት፤የኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ የወለደው ነው”ማለታቸውን የፍኖት ዘገባ ያመለክታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide