በኤፈርት ንብረቴን ተነጠኩ ያሉት ባለሃብት የድርሻቸውን ጠየቁ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 4/2010) የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ንብረት በሆነው ኤፈርት ንብረቴን ተነጠኩ ያሉት ባለሃብት ድርሻቸውን ለማስከበር አቤቱታ አቀረቡ።

የአዲስ መድሃኒት ፋብሪካ ጠንሳሽና በኋላም የ60 በመቶ ባለድርሻ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ ጓዴ ሙሉ በሙሉ ድርሻቸው በሕወሃቱ ኤፈርት በመነጠቃቸው መብታቸውን ለማስከበር በእንግሊዝና በአሜሪካ ፍርድ ቤት ያደረጉትን ጥረት ለኢሳት ገልጸዋል።

በደርግ ዘመነ መንግስት የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ንግዱ አለም በመግባት ስኬታማ ጉዞ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ ጓዴ የኢሕአዴግ መንግስት ሲገባ የመድሃኒት ፋብሪካ ለማቋቋም አቅደው መንቀሳቀሳቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ መድሃኒት ፋብሪካ ጠንሳሽ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ ጓዴ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት በወቅቱ ለፋብሪካቸው ፈቃድ ለማውጣት እክል ሲገጥማቸውና እንደማይቻል ሲነገራቸው የሕወሃቱ መሪ የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋና ሌሎች ሽርክና ጠይቀው አቶ ስብሃት ያመጧቸው ሰው ፕሮጀክቱን በሽርክና ሲቀላቀሉ ፈቃድ መገኘቱን አስታውሰዋል።

ፋብሪካው ሲታቀድ ድሬደዋ ወይንም አስመራ እንደነበር የገለጹት አቶ ሙሉጌታ ጓዴ የሕወሃት ሰዎች ሲገቡበት ወደ አዲግራት መወሰዱን ገልጸዋል።

አቶ ስብሃት የማጧቸው ሰው 40 በመቶውን ሲይዙ አቶ ሙሉጌታ ጓዴ 60 በመቶ ይዘው ስራው እንዲቀጥል ተደረገ ይላሉ።

በሂደትም የግለሰቡ ድርሻ ወደ ኤፈርት እንዲዛወር መደረጉንና በኋላም በግፊትና በጫና ከሳቸውም ድርሻ ኤፈርት 11 በመቶ በመውሰድ ከግማሽ በላይ መቆጣጠሩን ዘርዝረዋል።

በዚህ ሒደት ውስጥ አቶ ስዬ አብርሃና አቶ አባዲ ዘሙ ዋና ተዋናዮች እንደነበሩም ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

የሕወሃት ሰዎች ከፋብሪካው ላይ ሙሉ በሙሉ የበላይነት ለማግኘት ከአክሲዮን ድርሻ ባሻገር ያደረጉትን ተጽእኖና የትግራይ ፍርድቤቶች ያደረሱባቸውን በደል ዘርዝረዋል።

ሁኔታዎችን መቋቋም ሲያቅታቸው በውጭ ሐገር ሆነው ጉዳዩን ሲከታተሉ የሌሎች ድርጅቶቻቸው ሒሳብ ጭምር እንዲታገድ በማድረግ ከልጅነት ጀምሮ ከተሳተፉበት የንግድ ሒደት ውስጥ ተገፍተው መውጣታቸውን ተናግረዋል።

መነሻው ላይ ብቻ በጥሬ ገንዘብ 25 ሚሊየን ብር ያፈሰሱበትን የመድሃኒት ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ ተነጥቀው ከሃገራቸው ተሰደው አሜሪካ ለመኖር የተገደዱት አቶ ሙሉጌታ ጓዴ የነበረውን ሒደት ከመነሻው ጀምሮ በዝርዝር ለኢሳት ገልጸዋል።

በአሜሪካና በእንግሊዝ ፍርድ ቤቶች ክስ መስርተው መሟገታቸውንም ገልጸዋል።

ሕወሃት የኤፈርት ኩባንያዎችን በከፊል ለሕዝብ ለማስተላለፍ መወሰኑን በተመለከተም በሳምንቱ መጀመሪያ ለሕወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በጻፉት ደብዳቤ በተቋማቱ ላይ ያለኝን የይገባኛል ጥያቄ አብረው ሊገልጹ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በነበረው ሁኔታ ሐገሬን ለመልቀቅ እንዲሁም ዜግነቴን ለመቀየር ተገደድኩ በማለት የተቆጩት አቶ ሙሉጌታ ጓዴ ከኢሳት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ የፊታችን ረቡዕ እናቀርባለን።