በኢትዮጵያ የዳቦ ታሪፍ መመሪያ ወጣ

ህዳር 6 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለፉት 20 ዓመታት የግብርና ምርትን 40 በመቶ አሳድጌያለሁ የሚለው የአቶ መለስ መንግስት፤ ልክ እንደ ታክሲ ሁሉ ለዳቦም- ታሪፍ ማውጣቱን የዘገበው፤ ፍኖተ-ነፃነት ነው።

የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሕዳር 2 ቀን 2004 ዓመተ ምህረት ባወጣው የታሪፍ መመሪያ በከተማዋ በሚገኙ ዳቦ ቤቶች 100 ግራም ዳቦ በ1 ብር ከ20 ሳንቲም፣200 ግራም ዳቦ በ2 ብር ከ40 ሳንቲም እና፣300 ግራም ዳቦ በ3 ብር ከ60 ሣንቲም እንዲሸጥ ወስኗል።

ከዚህ መመሪያ ውጪ ሲሸጥ የሚሸጥ ዳቦ ቤት ካለ ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኝው መንግስታዊ አካል አቤቱታውን እንዲያሰማ ወይም ጥቆማውን እንዲያቀርብ የሚያሳስብም  መልዕክትም
አብሮ  ተለጥፏል፡፡

የተወሰኑ የከተማዋ ዳቦ ቤቶች በአዲሱ ታሪፍ  መሠረት  ዳቦ ጋግረው እየሸጡ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል ታሪፉ ሳይወጣ “ከግራም በታች ሽጣችሁዋል”ተብለው  በአስተዳደራዊ እርምጃ የታሸጉት በርካታ ዳቦ ቤቶች ግን፤ አሁንም እንደተዘጉ ናቸው።

ከዚህም ባሻገር ታላላቅ የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካዎች በስንዴ እጥረት  ምክንያት ሥራቸውን ካቆሙ ወራት መቆጠራቸው ታውቋል። ሸዋ ዳቦ በስንዴ እጥረት ምክንያት  በመዲናይቱ ካሉት 65 ዳቦ ቤቶች 45 ቱን እንደዘጋና በቀን እስከ 350 ኩንታል ዱቄት የመጋገር አቅም ያለውን ፋብሪካውን እንዳሸገ ሥራ አስኪያጁ መናገራቸው ይታወሳል።

መንግስት  ለእያንዳንዷ ኩንታል 200 ብር ድጎማ  በማድረግ ከውጪ የገዛው 900 ሺህ ኩንታል ስንዴ ሰሞኑን ዝቅ ባለ ዋጋ እንዲከፋፈል ሲደረግ የኢህአዴግ ሹመኞች፦ “እርምጃው የህብረተሰቡን መሰረታዊ ችግር የቀረፈ ነው” ሲሉ ቢሰሙም፤ ሳምንታት ሳይሞላ ችግሩ እየከፋ መምጣቱና ትርምሱ ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።