በኢትዮጵያ የተከሰተው የለውጥ ሂደት ስጋቶችንም ያዘለ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2011)በኢትዮጵያ የተከሰተው የለውጥ ሂደት ተስፋን ይዞ የመምጣቱን ያህል በተቃራኒው ስጋቶችንም ያዘለ እንደሆነ በአፅንኦት መገምገሙን የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ኢሕአዴግ በመግለጫው እንዳለው ለዉጡ አሁንም ህዝባዊ መሰረት ይዞ በኢህአዴግ እየተመራ ያለ ቢሆንም በፀረ ለውጥ አስተሳሰብ አራማጆች በተቀናጀ መንገድ እየተመሩ ተግዳሮት እየፈጠሩ ናቸው።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ላለፉት 3 ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ያወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በድርጅቱ ውስጥም ሆነ በለዉጡ ሂደት የተሟላ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የለም።

የታችኛው መዋቅርም ለውጡን በተሟላ መልኩ አለመደገፉ እና በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ያሉ የአካሄድ ዝንፈቶችና የእርስ በርስ መጠራጠር በግልፅ ተነስተው ትግል ተደርጎባቸዋል ብሏል።

እናም እነዚህን ችግርች በቀጣይ እንዲስተካከሉ ለማድረግና ለውጡን ለማስቀጠል የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ  መግባባት ላይ መድረሳቸውን መግለጫው አመልክቷል ።

መግለጫው እንዳለው ከለውጡ በተቃራኒ ያሉ ሃይሎች ህዝቡን ለማደናገርና ድጋፍ ለማግኘት እንዲያመቻቸው ለውጡን ተከትሎ ያሉ የአመራር ግድፈቶችን፤ እንዲሁም ማንነትንና ሌሎች አጀንዳዎችን ምክንያት በማድረግ ፅንፈኛ አካሄድ እየተከተሉ ናቸው።

የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም ሲሉም በዜጎች ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስና ዜጎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ እያደረጉ ናቸው ሲልም ወንጅሏል።

የለውጡ አደናቃፊ ሃይሎች በህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር በመታገዝ ግጭትና መፈናቀል እንዲፈጠር፣ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በመሰሉ የኢኮኖሚ አሻጥሮች በመሳተፍ ለውጡን ለመግታት እየተረባረቡ እንደሚገኙም ገምግሟል።

አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ፅንፈኝነትን በመስበክ የቆየውን የህዝቦች አንድነት በመሸርሸርና የህግ የበላይነትን ባለማክበር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ነው ያለው።

እናም ከዚህ ተግባራቸው በመቆጠብ በሃሳብ ልዕልና እና በውይይት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መጎልበት ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

በሀገሪቱ አሁን ላይ ጎልተው የሚታዩት ተግዳሮቶች የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር፣ የስራ ተልዕኮ አፈፃፀም መዳከም እና በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ እሴት መታጣት መሆናቸውን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስምሮበታል።

የመገናኛ ብዙሃንም የህዝቦች አንድነት የሚያጠናከርበትንና የተሻለች ሀገርን ለመገንባት የሚያስችል አተያይ በመፍጠር በኩል ተዓማኒነታቸውን የሚፈታተን የስርጭት ችግር እንዳለባቸው ኮሚቴው ገምግሟል።

ለዉጡ ያስፈለገው በትናንቱ ለመቆዘም ሳይሆን ወደፊት ለመወንጨፍ ቢሆንም ሚዲያው የህዝቡን አተያይ በመቅረፅ ረገድ ግን ብዙ ይቀረዋል ብሏል- የኢሕአዴግ መግለጫ።

በተለይ ደግሞ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ አሉታዊ ሚናው እየጎላ መምጣቱን ገምግሞ ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባ አመላክቷል።

በኢኮኖሚው መስክ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ  መኖሩን የገለጸው ኢሕአዴግ ይህም  ከፍተኛ የስራ አጥነት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የብድር ጫና ማስከተሉንና አሁንም መዋቅራዊ ችግሩ ያልተፈታ መሆኑንም ገምግሟል።