በኢትዮጵያ የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተባቸው ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች፤ ዐቃቤ ህግ ባቀረበባቸው የመጀመሪያ ምስክር ቃል መሳቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ

ኢሳት ዜና:- እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኞቹ ላይ የመጀመሪያው የአቃቤ ህግ ምስክር ኢንስፔክተር መሀመድ አህመድ የተባለ የፖሊስ አባል ነው። ኢንስፔክተር መሀመድ፤ ጆሀን ፐርሰን እና ማርቲን ሽብዬ የተባሉት ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች የኦጋዴ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ተዋጊዎችን የሚያሰለጥኑ ናቸው  በማለት ነው የመሰከረው።

የኢንስፔክተሩ ምስክርነት ከተሰማ በሁዋላ ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኞቹን ፦የኦጋዴ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ተዋጊዎችን ስለመርዳትና ስለማሰልጠን በተሰማው ምስክር ላይ ያላቸውን አስተያዬት ይናገሩ ዘንድ ሲጠይቃቸው ሁለቱም እየሳቁ ራሳቸውን በመነቅነቅ ምስክርነቱ ውሸት ነው ማለታቸውን  አሶሲየትድ ፕሬስን በመጥቀስ ቢቢሲ ዘግቧል።

ሁለቱ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት የቀረቡትም፤ነጠላ ጫማ ተጫምተውና እጃቸውን በሰንሰለት ታስረው እንደሆነ የዜና አገልግሎቱ ጠቁሟል።

በዕለቱ አቃቤ ህግ ከዚህም በተጨማሪ የቪዲዮ ማስረጃ ለማቅረብ የሞከረ ቢሆንም፤ቪዲዮው የት እንደተቀረፀ? እና መቼ እንደተቀረፀ? ግልፅ ካለመሆኑም በላይ ፈፅሞ ድምፁ የማይሰማ በመሆኑ  ፍርድ ቤቱ
አስቁሞታል።