በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ ወድቋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 28/2011)በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ በመውደቁ ሕግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚፈጸም ተገለጸ።

አወዛጋቢ የሆኑትና በአፋኝነታቸው የሚጠቀሱ አዋጆች በዚህ አመት እንዲሻሻሉ ዝግጅት መጠናቀቁም ተመልክቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 አዲስ አመት የመጀመሪያ ስብሰባውን ሲያደርግ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር እንዳመለከቱት የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋቱ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በየአካባቢው ያለውን ግጭትና የተከተለውን የሰዎች ሞት የዘረዘሩት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ መውደቁንም አመልክተዋል።

ሃገሪቱን ከቀውስ ለመታደግና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ መንግስት ሕግ የማስከበሩን ተግባር እንደሚወጣ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋቱ ተግባር እንደሚቀጥል፣አፋኝ የሆኑ ህጎች እንደሚሻሻሉና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናግረዋል።

በተለይም የጸረ ሽብር ሕግ፣የመገናኛ ብዙሃንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አዋጅ የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑንና በዚህ አመትም የተሻሻሉት አዋጆች እንደሚጸድቁ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግስቱ አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማዋቀር ማለትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችንና ሌሎች ተቋማትን የመከለሱ ስራ መጠናቀቁንም አመልከተዋል።

ይህም በቅርቡ ለምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር የተመለከተ አዋጅ ዛሬ አጽድቋል።

42 የነበሩ መስሪያ ቤቶችንና አደረጃጀቶችን ወደ 38 ዝቅ ማድረጉም ታውቋል።