በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያጋልጥ ዘጋቢ ፊልም ዛሬ ተመረቀ

 መጋቢት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከአራት የተለያዩ አገሮች ተሰደው በኔዘርላንድስ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞችን በመጠቀም የተሰራው ፊልም ዛሬ ሄግ በሚገኘው የፊልም አዳራሽ በርካታ እንግዶችና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ተመርቋል።

ኢትዮጵያን በመወከል በፊልሙ ውስጥ የተሳተፈው የኢሳት ጋዜጠኛ የሆነው ፋሲል የኔአለም ነው። ሊዙ ፣ ፋቲ እና ጅግሜ የተባሉ ከቻይና፣ ከሊቢያና ከቡታን የመጡ ስደተኞችም በፊልሙ ውስጥ ተሳትፈዋል።

የ90 ደቂቃ እርዝመት ባለው ፊልም ውስጥ የጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ግለ ህይወት፣ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች መከበር እያደረገው ያለው ተጋድሎና ኢሳት በኢትዮጵያ ትግል ውስጥ እየተጫወተ አለው ሚና ተካትቷል።

በፊልሙ ውስጥ በአለም ላይ ታዋቂ የሆኑት የአለማቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቢ ህግ የሖኑት ሞሪስ ኦካምፖ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር አንቶኒዮ ጉቴሬስ፣ የአውሮፓ ህብረት አባል የሆኑት ሚስ አና ማሪያ ጎሜዝ፣ የጀርመን የፓርላማ አባል ሚ/ር ቲሎ ሆፕ እንዲሁም የቀድሞው የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒሰትርና ሌሎችም የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጽመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ፣ ለመለስ መንግስት የሚሰጠው የውጭ እርዳታ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭቆናን እያስፋፋ መሆኑ እንዲሁም ኢሳት ለኢትዮጵያ ህዝብ ብርሀን መሆኑ ተወስቷል።

በተመሳሳይም በሊቢያና እና በቻይና የሚፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቷቸዋል።

ፊልሙ በየአገራቱ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ከማጋለጥ ባሻገር የአውሮፓ አገራት በሚከተሉት የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ተጽኖ ያሳድራል ተብሎ ታምኖበታል። ከፊልሙ ዝግጅት በሁዋላ ከተመልካቹ ለጋዜጠኛ ፋሲል እና ለሊቢያዊው የሰብአዊ መብት ተመጓች ለሆነው ፋቲ ከተመልካቹ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል።

ከምረቃው ስነስርአት በሁዋላ ፋሲል በሰጠው አስተያየት ” በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸመውን ግፍ አለም እንዲያውቀው የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ በመቻሌ ደስ ብሎኛል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸመው  በደል ቃላት ሊገልጡት ከሚችሉት በላይ በመሆኑ ብዙ ስራዎችን መሰራት ይጠበቅብናል። ዛሬ የተወሰነው የአለም ክፍል አውቆናል። ጠንክረን ከሰራን ነገ ሌላውም የአለም ክፍል ያውቀናል። የአውሮፓ መንግስታት ፊልሙን ተመልክተው በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን ፖሊሲ ዛሬ ይቀይራሉ ብዬ የማስብ የዋህ ባልሆንም፣ በዲፐሎማሲው ረገድ ጫና ለመፍጠርና ኢሳትን ለአለም ለማስተዋወቅ ይረዳል ብየ አስባለሁ። ፊልሙ  የእኔ የልፋት ውጤት ብቻ ሳይሆን የኢሳት ጋዜጠኞች፣ የኢሳት ማኔጅመንትእና መላው የኢሳት ደጋፊዎች ቆርጠው በመታገላቸው ያስገኙት ውጤት ነው” ብሎአል።

Refugees who needs them? የሚል ርእስ የተሰጠው ፊልም ዋና ዳይሬክተር አሜሪካዊው ማይልስ ሮስቶን ነው። ማይልስ ከምርቃቱ በሁዋላ ለኢሳት በሰጠው ቃለምልልስ በስራው ደስተኛ መሆኑን ገልጧል። የኢትዮጵያ መንግስት ከእንግዲህ አሸባሪ ብሎ ሊመዘግበው እንደሚችልም አክሎአል።

ፊልሙ ጄኔቫ ውስጥ በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ይቀርባል።

በመጪዎቹ ሶስት ቀናትም ዘ   ሄግ በሚገኘው ቲያትር ሄት ስፓው ውስጥ ይተላለፋል። በተለያዩ የአውሮፓ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንደሚቀርብ ፊልሙን ከሚያሰራጨው ኩባንያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide