በኢትዮጵያ ባንኮች እና በፍትህ አካላት መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል

ግንቦት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፍትህ አካላት የደንበኞቻቸውን ምሥጢር እንዲያወጡ በሚያሳርፉባቸው ጫና ባንኮች በአሠራራቸው ላይ ከፍ ያለ ችግር ተጋርጦባቸዋል።

እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤አንዳንድ የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ አባላት ለባንኮች የደንበኛ ምሥጢር እንዲገለጽላቸው በሚያቀርቡት ጥያቄና- ባንኮችም ጥያቄውን ለመመለስ የደንበኛው ፈቃድ ወይም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲቀርብላቸው በሚያነሱት ጥያቄ የተነሳ፤ አለመባባት ከተፈጠረ ሰንበትበት ብሏል።

በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ባለፈው ረቡዕ ችግሩ ላይ ያነጣጠረ አውደ ጥናት ለማካሄድ ተገዷል።

በዐውደ ጥናቱ ፦“የደንበኞችን ምስጢር ከመጠበቅ አንጻር የባንኮች ሚና ምን መሆን አለበት?” በሚል ርዕስ   በማኅበሩ ሕግ አማካሪዎች ኮሚቴ ጥናታዊ ጽሑፍ ሲቀርብ እና  ውይይት  ሲካሄድ ፤ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ፖሊሶች፣ ዓቃቤ ሕጎችና ዳኞች  ተሳትፈው ነበር።

ዓውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ፤ ከባንኮች መረጃ ከሚፈልጉ ተቋማት መካከል የፍትሕ አካላት እንደሚገኙበት በመጥቀስ፣  ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ በሕግ አግባብ ከተጠቀሰው ሥርዓት ውጪ የደንበኞችን መረጃ ከመጠየቅ ጋር በተያያዘ በባንኮች እና በፍትህ አካላት መካከል ችግሮች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

በዕለቱ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት አቶ ኤፍሬም ኃይለ ማርያምና አቶ ደምሰው አበበ  የተባሉ የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ የደንበኞችን መረጃ ወይም ምሥጢር የመጠበቅ ግዴታ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 26 መሠረት፤ ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱና ግላዊነቱ የመከበር መብት እንዳለው ጠቅሰው፣ በዚህም ምክንያት ማንኛውም ሰው መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ ከመመርመር እንደሚከለከል እንዲሁም ሌሎች በግሉ የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች እንደሚከበሩና እንደማይደፈሩ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል ረገድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ባንኮች ሕግ እስከፈቀደላቸው ድረስ  ማገዝ እንደሚገባቸው   ያብራሩት ጥናት አቅራቢዎቹ፣ በዚህ አግባብ ፖሊስና ባንኮች ለረዥም ዓመታት በመተጋገዝ ሲሠሩና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ አባላት የደንበኛ ምሥጢር እንዲገለጽላቸው ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ባንኮች የደንበኛውን ፈቃድ ወይም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተያይዞ እንዲቀርብላቸው ሲጠይቁ አለመግባባት እየተፈጠረ መምጣቱን እና ይህም  በአሠራር ላይ እንቅፋት ማስከተሉን የህግ ባለሙያዎቹ አልሸሸጉም።

የህግ ባለሙያዎቹ አያይዘውም፦በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 22(3) መሠረት ማንኛውም ባንክ ከሥራው ጋር በተያያዘ ምክንያት ያወቀውን ወይም የያዘውንና የማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት የሚመለከት መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ ለሚገኝ ለማንኛውም ሰው መስጠት እንደማይችል በማስገንዘብ፣ ባንኮች የግለሰብ ሚስጥርን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም በልዩ ሁኔታ አስገዳጅ ከሆኑ ሕግጋት ውጭ ፤መስጠት እንደማይችሉ አስገንዝበዋል፡፡

በባንኮቹ ላይ በዋነኝነት እንቅፋት እየተፈጠረ ያለውም፤ ከሽብርተኝነት እና ከሙስና ጋር በተያያዘ ፖሊሶች እና ዓቃብያነ-ህጎች ያለ ፍርድ ቤት መያዣ የግለሰቦች የሂሳብ ምስጢር እንዲገለፅላቸው በመጠየቃቸው ነው።

የአቶ መለስ መንግስት  በቅርቡ ባወጣው  አዋጅ ፤ አንድ ግለሰብ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ በባንክ ሲያስቀምጥ ባንኮች ለመንግስት ሪፖርት ማቅረብ እንዳለባቸው  መደንገጉ ይታወሳል።

በወቅቱ ምንዛሬ መሰረት 200 ሺህ ብር ማለት፤ 8 ሺህ 930 ዩሮ ማለት ነው።

ይህ ማለት አንድ ኢትዮጵያዊ ወይም የውጪ ዜጋ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ መንግስት ወይም ሌሎች የመንግስት አካላት ሳያውቁበት በምሥጢር ከ 9 ሺህ ዩሮ በላይ ማስቀመጥ አይችልም ማለት ነው።

ይህ አዋጅ  በተለይ ወደ አገራቸው ሄደው በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች በተሰማሩ እና ወደፊትም ለመሰማራት በሚያስቡ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን(ዲያስፖራዎች)  ላይ ያለው ኢኮኖሚያዊ አደጋ እና የሚፈጥረው የደህንነት ሥጋት ከፍ ያለ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአቶ መለስ መንግስትም ሆነ የፍትህ አካላቱ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌን በሚፃረር መልኩ ባንኮች  ከደንባቸውና ከመመሪያቸው ውጪ እንዲሠሩ ጫና እያበዙባቸው ያሉትም፤ “ሽብርተኝነትን”እና “ሙስናን ለመከላከል በሚል ሽፋን እንደሆነ ታውቋል።

በዓለም ላይ በአፋኝነቱ እና በጨቋኝነቱ ተወዳዳሪ የለውም በተባለለት የኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር ህግ ፤ መንግስት ወይም አንድ ፖሊስ ያለ ምንም መረጃ እና ማስረጃ “ በሽብርተኝነት ጠርጥሬሀለሁ” ያለውን ግለሰብ  ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊያስረው፣ እስከ 4 ወር ድረስ ፍርድ ቤት ሳያቀርብና ክስ ሳይመሰርት ሊመረምረው፣ ህገ-መንግስቱን እና የባንክ አሰራር መመሪያን በጣሰ መልኩ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፋይናንስ ምሥጢሩን ሊያውቅበት አለያም ሊያዘጋበት  ይችላል።

የፀረ-ሽብር ህጉ መደንገጉን ተከትሎ በኢትዮጵያ  የሽብርተኝነት ክስ እየተመሰረተባቸው ያሉት ደግሞ ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እና ጋዜጠኞች መሆናቸው ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide