በአፋር ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 7/2011)ሰመራን ጨምሮ በአፋር ዘጠኝ ወረዳዎች ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ።

የክልሉ አመራሮች ለውጡ ለአፋር ህዝብ እንዳይደርስ አድርገዋል፣ የአፋር ህዝብ በሃብቱ እንዳይጠቀም ተደርጓል፣የህወሃት ጣልቃ ገብነት በአፋር ክልል ይቁም የሚሉ መልዕክቶች የተላለፉበት የተቃውሞ ሰልፍ በሌሎቹም የክልሉ ወረዳዎች እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።

በአፋር ክልል የህወሀት ባለሀብቶች የጨውና የማዕድን ስራዎችን መቆጣጠራቸው በአፋር ወጣቶች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

በቅርቡ ከየወረዳው የተወከሉ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለማነጋገር እቅድ መያዛቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

አፋሮች ዛሬ በዘጠኝ ወረዳዎች ያደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ለሁለት አካላት መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ እንደሆነ ይገልጻሉ።

አንደኛው የአፋርን ክልል ለሚመሩ ባለስልጣናት ሲሆን በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ነው።

በህወሀት ተጽዕኖ ስር ያለው የአፋር ክልል አመራር የህዝቡን ስቃይ እያባባሰው ነው፡  ለውጥ እያደናቀፈ ነው የሚል ተቃውሞ ያነሳው የአፋር ህዝብ አመራሩ ከስልጣን እንዲነሳ ድምጹን እያሰማ ይገኛል።

ሁለተኛው መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደሆነ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተስተጋብቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አፋርን ዘንግተዋል፡ የለውጡ ሽታ እንዳይደርሰን ባደረጉ የክልሉ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰድ አልቻሉም የሚል ወቀሳ ያዘለ መልዕክት ነው ዛሬ ሲሰማ የነበረው።’

በአፋር የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም የህወሀት ባለሀብቶችን ተስፋፊነት በሚቃወሙ የክልሉ ተወላጆች ላይ በስውር ከአፈኣና ጀምሮ የተለያዩ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን የጠቀሱት የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች በዛሬው ዕለት በዘጠኝ ወረዳዎች የተድረገው ሰልፍ የአፋር ህዝብ ትዕግስት ማለቁን ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።

ሰሞኑን በአፋር የአንድ የህወሀት ባለሀብት የጨው ማምረቻ ድርጅት በህዝቡ ተቃውሞ መዘጋቱን ተከትሎ ውጥረት የነገሰ ሲሆን በህወሀት የሚጠመዘዘው የአፋር ክልል አስተዳደር ገንዘብ በመክፈል የተዘጋው የጨው ድርጅት እንዲከፈት የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማስደረጉ መዘገባችን ይታወሳል።

መንግስት በአስቸኳይ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ በ32ቱም የአፋር ክልል ወረዳዎች የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግም አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

የአፋርን ገዢ ፓርቲ በመቆጣጠ ተፈጥሮአዊ ሀብቱን ለህወሀት ሰዎች አሳልፈው እየሰጡ ያሉ የአፋር ክልል አመራሮች በሌሎች ክልሎች የተጀመረውን ለውጥ እያደናቀፉት መሆኑን በመግለጽ በሚቀጥለው ሳምንት ከየወረዳው የተወከሉ 64 ወጣቶች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመደን ለማነጋገር ወደ አዲስ አበባ እንደሚያመሩ ለማወቅ ተችሏል።

የተጀመረውን ለውጥ በማደናቀፍ በጋምቤላም ተመሳሳይ ተቃውሞ እየተደረገ ሲሆን አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ለፌደራል መንግስቱ ጥያቄ በመቅረብ ላይ ይገኛል።