በአዲስ አበባ አሽከርከሪዎች የነዳጅ ማደያዎችን አጨናንቀው ዋሉ

በአዲስ አበባ አሽከርከሪዎች የነዳጅ ማደያዎችን አጨናንቀው ዋሉ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 04 ቀን 2010 ዓ/ም) ቄሮ ለአንድ ሳምንት የጠራውን ነዳጅ አቅርቦት እቀባ ተከትሎ በአዲስ አበባ ነዳጅ ለመቅዳት የፈለጉ አሽከርከሪዎች ማደያዎችን አጨናንቀው ታይተዋል። ቄሮ ነዳጅ በሚያመላልሱ ቦቴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ካስጠነቀቀ በሁዋላ፣ በአገሪቱ የነዳጅ እጥረት ሊፈጠር ይችላል ብለው የሰጉ አሽከርካሪዎች፣ ነዳጅ ማደያዎችን አጨናንቀው ታይተዋል።
ምንም እንኳ እስካሁኑ ሰአት ድረስ በነዳጅ ማመላለሻ መኪኖች ላይ ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ባንችልንም፣ ውሳኔው በትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ ታይቷል። አንዳንድ የነዳጅ መሸጫ ማደያዎችን ነዳጅ መጨረሳቸውን የሚያመለክቱ ማስታወቂያዎችን ለጥፈው ታይተዋል።
ቄሮ ለአንድ ሳምንት የጠራውን አድማ የሚተላለፍ የነዳጅ ጫኝ አሽከርካሪ ጉዳት እንደሚደርስበት አስጠንቅቋል። የአድማው አላማ በአገሪቱ ላይ የነዳጅ እጥረት በመፍጠር አገዛዙ ለሚነሱ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥ ማስገደድ ነው።

በሌላ በኩል በአገሪቱ የቀጠለው የለውጥ ጥያቄ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው። በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ከሚታየው የዋጋ ጭማሪ በተጨማሪ እቃዎች ከገበያ መጥፋታቸው ህዝቡን ስጋት ላይ ጥሎታል። በተለይ በስኳርና በዘይት አቅርቦት ላይ የሚታዬው ችግር ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሷል። የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮም መረጃውን መደበቅ ወደ ማይችልበት ደረጃ ደርሷል። እጥረቱ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ የተከሰተ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል። በተለይ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን እቃ መጠን እንዳሳነሰው ባለሙያዎች ይናገራሉ። የእቃዎች እጥረት ደግሞ የዋጋ ንረትን አስከትሏል።
በአገሪቱ የተፈጠረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በህጋዊ መንገድ ገንዘባቸውን እንዲልኩ ኢምባሲዎች ስራዎችን እንዲሰሩ ታዘዋል። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጠሩትን የውጭ ምንዛሬ ማእቀብ ተከትሎ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን በባንክ ከመላክ ይልቅ በሌሎች መንገዶች እየላኩ ነው። ኢምባሲዎችም በህገ ወጥ መንገድ ገንዘባቸውን የሚልኩ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸው እንደሚሰረቅባቸው እያስፈራሩ፣ ገንዘብ በባንኮች እንዲላክ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።